ከንቲባውን ጨምሮ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች የሚገኙበትን ህንፃ የሚጠብቁ 20 የጥበቃ ሰራተኞችን የከንቲባ ጽ/ቤት ከድሬዳዋ ፖሊስ አካዳሚ ጋር በጋራ በመሆን ለ5 ተከታታይ ቀናት በተግባርና በንድፈ ሃሳብ የተደገፈ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
ወ/ሮ ሰአድያ አዋሌ በድሬዳዋ አስተዳደር የመልካም አስተዳደር የህዝብ ቅሬታ ፣አቤቱታ ሰሚ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የከንቲባ ጽ/ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ስለ ስልጠናው አስፈላጊነት ሲገልፁ ፤ በተለምዶ ፋይናንስ ተብሎ የሚጠራው ህንፃ ላይ ክቡር ከንቲባና ምክትል ከንቲባውን ጨምሮ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች የሚገኙበት በመሆኑ በተቋሙ ስር ያሉ የጥበቃ ሰራተኞች ንቁና ህንፃውን የሚመጥን የጥበቃ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል፡፡
የድሬዳዋ ፖሊስ አካዳሚ ዳይሬክተር ኮማንደር ጌታቸው መገርሳ በበኩላቸው የከተማ ደህንነት ስራ የሚጀምረው ከተቋማት ጥበቃ በመሆኑ የጥበቃ አባላት ወታደራዊ ስልጠና የሰለጠኑና ስራቸውን በበቂ ሁኔታ የሚያውቁ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ኮማንደሩ አክለውም ስልጠናው አጠቃላይ ተቋማት እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው በንድፈ ሃሳብ እንዲሁም የጦር መሳሪያ አጠቃቀምና አያያዝ ተኩስን ጨምሮ በተግባር ልምምድ ድረስ ለ 5 ተከታታይ ቀናት በመስጠት ፈትኖ ፈተናውን ያለፉትን እውቅና እንደሚሰጥም ነው የገለፁት፡፡
የከንቲባ ጽ/ቤት የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብሩክ አዳነ እንደ መነሻ የከንቲባ ጽ/ቤትና ተጠሪ ተቋማትን የጥበቃ ሰራተኞች በስነ ምግባር ፣ በመሳሪያ አጠቃቀም ተኩስን ጨምሮ ወቅቱን የጠበቀ ስልጠና በመስጠት የተቋሙን ደህንነት ለማረጋገጥ በሁለት ዙር የሚሠጥ ስልጠና ማዘጋጀታቸውን ጠቁመው ፤ ሌሎች ተቋማትም ይህንን ተግባር እንዲያስቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።


