በደን ልማት፣ በጥምር ደን ልማትና በወንዝ ዳርቻ ልማት ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ::

ማህበረሰቡ የተሻለ የተፈጥሮ ሃብት ያላት አገርን ለነገው ትውልድ የማስረከብ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው ተገልጿል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች በጋራ እየተከናወነ በሚገኝው የSUNCASA ፕሮጀክት በሚተገበርባቸው የገጠር ቀበሌዎች በደን ልማት፣ በጥምር ደን ልማትና በወንዝ ዳርቻ ልማት ለአመራሩ ባለሙያዎችና ነዋሪዎች የግንዛቤ ማዳበሪያ መድረክ አካሂዷል።

የድሬዳዋ የአስተዳደር አካባቢ አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱ መሀመድ ድሬዳዋ በተደጋጋሚ ያጠቃት የነበረውን ጎርፍ በዘላቂነት ለመከላከል በተሰራው ስራ በዚህ አምስት ዓመት ብቻ በገጠር በከተማ ያለውን የአካባቢውን ስነምህዳር መቀየር መቻሉን በመደረኩ ላይ ገልፀዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ፣የአካባቢ ጥበቃ እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ በስፋት ሁሉንም ነዋሪዎች በማስተማር ከአጋር ድርጀቶች ጋር ተቀናጅቶ በመሰራቱ ለውጥ መምጣቱን አቶ አብዱ ተናግረዋል።

የባለስልጣኑ የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር በበኩላቸው በአስተዳደሩ በተሰራው የተቀናጀ ስራ የአስተዳደሩ ስነ-ምህዳር መሻሻል እያሳየ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ድሬዳዋ ዝናብ አጠርና ለጎርፍ ተጋላጭ እንደመሆኗ አካባቢን መንከባከብና መጠበቅ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት በከተማም ሆነ በ38ቱም ገጠር ቀበሌዎች የሚገኝው የአስተዳደሩ ነዋሪ በኔነት ስሜት በተግባር በመሳተፍ ላይ እንደሚገኝ አቶ ማስረሻ አስታውቀዋል።

ድሬዳዋ ላይ ይደርስ የነበረውን የጎርፍ አደጋ ስጋት ለመቀነስ በበጎ ፍቃደኝነት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ በመሳተፍ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ እየሰሩ እንደሚገኙ በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ ያነጋገርናቸው ተሳታፊዎች ገልፀውልናል።

ድሬዳዋ ላይ ችግኝ መትከል አስፈላጊ መሆኑን በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ሁሉም ነዋሪ በአካባቢው የደን ሽፋንን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ።የSUNCASA ፕሮጀክት በድሬዳዋ መተግበሩ ደግሞ የጉዳቱን መጠን በግልጽ በማሳየት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ህዝብን አስተባብሮ በስፋት ለመስራት እያገዘ መሆኑን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ስልጠናው በፕሮጀክቱ የሚከናወኑትን የደን ልማት፣ የጥምር ደን ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት /buffer zone Development/ በተሻለ መተግበር የሚያስችል አቅም መፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተገልጻል፡፡ ስልጠናው በባለስልጣን መ/ቤቱ እና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ተሰጥቷል::መረጃውን ያደረሰን የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ነወ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *