የስራ ፈጣሪዎችን የእርስ በእርስ ትስስርና መደጋገፍ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ

ከዚህ ቀደም ኦርቢት ኢኖቬሽን ሃብ ለዘላቂ የስራ ስምሪት በአንተርነርሺፕ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ፕሮግራም ከድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የስታርት አፕ የስራ ፈጠራ ዕድል ተጠቃሚ ወጣቶችን ያሰለጠነ ሲሆን፤ በዛሬው እለትም ስልጠናውን ለወሰዱ ስራ ፈጣሪዎች እና በአጠቃላይም በድሬዳዋ ከተማ ለሚገኙ ስራ የመፍጠር ፍላጎት ላላቸው ወጣቶቸ የእርስ በእርስ ትስስር መፍጠሪያ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ኢንደስትሪ ዩኒቨርስቲ ሊንኬጅ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር እሸቱ መኮንን የዛሬው መድረክ ዋነኛ አላማ ስራ ፈጣሪዎችንና ስራ ፈጠራን ማበረታታት እንዲሁም የስራ ፈጠራ ስነ ምህዳርን ማስፋት ማዕከል ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዶ/ር እሸቱ አያይዘውም በስራ ፈጣሪዎች መካከል ትውውቅ መፍጠር፣ የግልና የመንግስት ባለድርሻ አካላት ቅርርብ እንዲፈጥሩ ማድረግ፣ የኦርቢት ኢኖቬሽን ሀብ አንድ ፕሮግራም ሆኖ እየሰራ የሚገኘውን የሲድ ፕሮግራምንና እያመጣ ያለውን በጎ ተፅኖዎችን ማስተዋወቅ እንዲሁም አዳዲስ የስራ ፈጠራዎችን ማበረታታት በተጨማሪም ችግር ፈቺ ሀሳቦችን ለማበርከት መድረኩ ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው ተናግረዋል።

የስራ ፈጣሪዎች ማህበረሰብ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እርስ በእርስ እየተደጋገፉ እንዲፈቱ ለማድረግም የዛሬው መድረክ ጉልህ ሚና እንዳለው ዶ/ር እሸቱ ጨምረው ተናግረዋል።

የሲድ ፕሮግራም በአምስት አመት ውስጥ ለአንድ ሚሊየን ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እየሰራ ሲገኝ፤ በዚህም ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች እና ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተር ፕራይዞች ላይ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል፡፡

ፕሮግራሙ በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ አማካኝነት የሚሰራ ሲሆን የሚመራውም በኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትውት ሲሆን ከኦርቢት ኢኖቬሽን ሃብ በተጨማሪ አሜሪካን ኮሌጅ ኦፍ ቴክኖሎጂ፣ ሆፕ ኢንተርፕራይዝና የኢትዮጲያን ኤር ላይንስ አቬሽን ዩኒቨርስቲ የፕሮግራሙ ተሳታፊ መሆናቸው ተገልጿል።

በኤደን ሳሙኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *