ኒያ ፋዉንዴሽን ጆይ የኦቲዝም ማዕከል በድሬዳዋ አስተዳደር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ስለኦቲዝም እና ተዛማጅ የአእምሮ እድገት እክሎች ላይ የኦቲዝም ተጠቂ ልጆች ላላቸው ወላጆች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በዛሬው ዕለት መስጠት ጀምሯል፡፡
የኒያ ፋውንዴሽን የጆይ ኦቲዝም ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ እሌኔ ዳምጠው ስልጠናው በዋነኝነት የኒያ ፋውንዴሽን የጆይ ኦቲዝም ማዕከል የምስረታውን 23ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው፤ የኦቲዝም ተጠቂ ልጆች ያላቸው 40 ወላጆች በስልጠናው እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ይሄም እናቶችን እንዲሁም በአጠቃላይ ወላጆችን ለማገዝ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ እሌኔ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲረዱና ኦቲዝም የፈጠሪ ቁጣ እንዳልሆነ ለማስገንዘብ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ወ/ሮ እሌኔ በኦቲዝም የተጠቁ ልጆችን መንከባከብና ማስተማር የሁሉም ማህበረሰብ ሀላፊነት እንደሆነ ጠቁመው የድሬዳዋ አስተዳደርም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ለሚገኘው ስራ አመስግነዋል፡፡
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ፤-ናታን ሸዋንግዛው


