በአስተዳደሩ በለሊት ታክሲ አሽከርካሪ ማህበር ከተቋቋመ አምስት አመታትን ያስቆጠረና ከአምስት መቶ በላይ ወጣቶችን ያቀፈ ማህበር ነው ።
ማህበሩ ከሚሰጠው የለሊት ታክሲ ከማሽከርከር አገልግሎት በተጨማሪም ከተማዋ በለሊት ሰላሟ እንዲጠበቅ ከፀጥታ አካላት ጋር በመስራት በበጎ ፍቃደኝነት የደም ልገሳ 14 ጊዜ በመለገስ ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
በዛሬው እለትም በድሬዳዋ ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያ በመገኘት ከ350 በላይ የማህበሩ አባላት ደም ለግሰዋል።
በደም ልገሳ መርሀግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአስተዳደሩ ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወ/ሮ ከሪማ አሊ እንደጠቀሱት የማህበሩ ወጣቶች የድሬዳዋን ጸጥታ በማስጠበቅ ረገድ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እያደረጉት ያለው ጥረት እጅግ የሚያስመሰግናቸው ከመሆኑ በተጨማሪም በደም ልገሳ መርሃ ግብር ላይም በየጊዜው የሚያደርጉት ድጋፍ ሌሎችም የሚያስተምርና የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል ።
የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው በአስተዳደሩ በወሊድ ምክንያት የሚከሰተው የሞት አደጋ ለመቀነስ ዋነኛው ደም መለገስ በመሆኑ በቀዳሚነት ወጣቶቹ በየ3 ወሩ ይህን በመለገሳቸው ሣቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ እናቶች መታደግ በመቻላቸው ሊመሰገኑና በቀጣይም ለሌሎች ተሞክሮ መቀመር ያለበት መሆኑንም ጠቍመዋል።
የድሬዳዋ ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮምሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው እንደገለፁት የሌሊት ታክሲ ማህበራት አባላት የሆኑ ወጣቶች በሰላምና በበጎነት ረገድ በሚያደርጉት ዘርፈ ብዙ ስራዎችና ጉልህ ድርሻ አመስግነው አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አስተላልፏል ።
በተዘጋጀው መርሀግብር የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች ለከተማው እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ የጎላ ከመሆኑ ባሻገር ድሬዳዋና አዋሳኝ እንደመሆና መጠን የደም ፍላጎትና አቅርቦት የተመጣጠነ ባለመሆኑ ትልቁን የደም ልገሳ የሚያደርገው ማህበሩ መሆኑን በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የፈውስ ህክምና ተሀድሶ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዶ ሙሜ ይናገራሉ።
አቶ አብዶ አያይዘውም የለሊት ለታክሲ አሽከርካሪዎች ለሌሎች ግንዛቤ እንዲሰጡ የማስቻል ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ በመግለፅ ።
የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ቃልኪዳን ፀሐይ እንደገለፀው ማህበሩ ከተመሠረተ አምስት አመታት ውስጥ አምስት መቶ አባላት ሲኖረው በበጎ ፍቃድ ስራዎች ለከተማው ማህበራዊ ሀላፊነት ከመወጣትም ባሻገር በደም ልገሳው በቀዳሚነት 350 አባላትን ይዞ 14 ጊዜ እየለገሱ መሆኑን አብራርቷል።ሌሎችም የእነርሱን ተሞክሮ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው በመግለፅ ።
በመርሃ ግብሩ ላይም 280 ዪኒት ደም ተሰብስቧል።
Dire tv


