የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ ስራዎችን በፍጥነት፣ በጥራትና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

በሀገር አቀፍ ደረጃ አምራች ኢንደስትሪውን ለመደገፍና ለማበረታታት መንግስት ባዘጋጀው የአምራች ኢንደስትሪ ፖሊሲ ዙሪያ በዛሬው ዕለት በዘርፉ ከሚገኙ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ ተካሄደ።

በመድረኩ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ፣ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ስራዎችን በመደጋገፍና ተቀናጅቶ መስራት የአምራች ኢንደስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ምክትል ከንቲባ አያይዘውም ከለውጡ አመታት ወዲህ የማኒፋክቸሪንግና ኢንደስትሪው ዘርፍ 5 ዓላማዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልፀው፤ በዚህም የማምረት አቅምን ማሳደግ፣ ከውጪ ሀገር የሚመጡ ምርቶችን መተካት፣ ወደ ውጪ ሀገር የሚላኩ ምርቶችን ማሳደግ፣ የስራ እድል መፍጠር እንዲሁም የኢኮኖሚ መዋቅራዉ ሽግግር መፍጠር መቻል መሆኑን ያብራሩ ሲሆን በአስተዳደራችንም እነዚህ አላማዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እተሰራ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በአስተዳደሩ ከ24 ሺህ በላይ የስራ ዕድልን በመፍጠር እንደተቻለም ም/ከንቲባ አንስተው የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና በሙሉ አቅሙ መስራት ሲጀምር ለ30 ሺህ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጠር ገልፀዋል።

በተጨማሪም በአስተዳደሩ የማምረት አቅምን በተመለከተ አሁን ካለበት 58 ፐርሰንት በማሳደግ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ድርሻ ማሳደግ እንደሚገባ አቶ ሀርቢ ቡህ ተናግረዋል።

በመጨረሻም የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ ስራዎችን በፍጥነት፣ በጥራትና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ በተጨማሪም የስራ አካባቢን ማስዋብ እንደሚያስፈልግ ም/ከንቲባ አቶ ሀርቢ አመላክተዋል

የቢሮው ምክትል ኃላፊና አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር በበኩላቸው በሀገራችን የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ መውጣቱ በሌሎች ሀገራት እየተተገበረ የሚገኘውን በቴክኖሎጂ የመጠቀም ልምድን ይበልጥ ለማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ቴክኖሎጂ ለመዋቅራዊ ሽግግር አይነተኛ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ በዚህ መልኩ ውይይት ማደግ ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳለው ገልጸው በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችንም ለመሙላት ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማዳበር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በኤደን ሳሙኤል

ፎቶ፤-አገኘሁ ሸዋረጋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *