በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የተመራ የሱፐርቪዥን ቡድን በድሬዳዋ አስተዳደር የተሰሩ የመሠረተ ልማት ስራዎች ጎበኙ።

በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሄለን ደበበ የተመራ የሱፐርቪዥን ቡድን የድሬዳዋ አስተዳደርን የመሠረተ ልማት ስራዎችንና የኮሪደር ልማት ሂደትን ጎብኝተዋል።

በሚኒስትር ዴኤታዋ የተመራው የልዑካን ቡድን በአስተዳደሩ የመሰረተ ልማት እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የስራ አፈፃፀም ላይ ያተኮረ ሪፖርት በማድመጥ በአካል ወርዶ የተከናወኑትን ስራዎች ላይ የመስክ ምልከታ አካሂዷል።

በጉብኝታቸው በኢንዱስትሪ መንደር የተጠናቀቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ፣ የመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ቢሮ ዲጂታላይዝድ አግልግሎት አሰጣጥ ፣ ካህ ሪል ስቴትን ፣ የድሬዳዋ ፖሊስ የሪፎርም እና የወንጀል መከላከል ስራዎችን ፣ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘነውን የሲቪክ ማዕከልን ፣ በመደመር ትውልድ መፅሃፍ ሽያጭ የሚገነባውን ቤተ መጻሕፍት ጨምሮ የድሬዳዋ የኮሪደር ልማት ገፅታን መመልከት ችለዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሄለን ደበበ በጉብኝቱ ማጠቃለያም በኮሪደር ልማት ስራው ላይ ከእቅድ እስከ ትግበራ የአመራሩ ክትትልና ድጋፍ አመርቂ እንደሆነ ገልፀው ህብረተሰቡም ስራውን በባለቤትነት በመውሰድ ከተፈለገው ቦታ ለመነሳት ያሳየው ቀናነት ሊደነቅ የሚገባ እንደሆነ አመላክተዋል።

አያይዘውም የመሰረተ ልማት አቅርቦት ሰጪ የሆኑት እንደ ውሃ ፣ መብራት እና ቴሌ ለስራው ያሳዩት ቅንጅታዊ መግባባት በሃላፊነት ተረክበው ለሚሰሩት ተቋራጮች እንደረዳቸው ጠቁመዋል።

እንደ መንግስትም ሆነ እንደ ፓርቲ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ትልቅ ትኩረት የተሰጠበት ጉዳይ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ያስታወሱ ሲሆን በመሬት ልማት የታየው የካዳስተር ስርዓት ፣ የዲጂታል ድሬ ኢ-ሰርቪስ ወደፊት ለታለመው የስማርት ሲቲ ግንባታ መሰረት ይጥላል ብለዋል።

የአስተዳደሩን ሰላም እና ደህንነት ከማስጠበቅ እንፃር በድሬዳዋ ፖሊስ የተመለከቱት የተደራጀ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተሞክሮ ወደ ሌሎች ከተሞች በማስፋት ሊሰራበት የሚገባ እንደሆነም አረጋግጠዋል።

የጉብኝቱ አላማ የድሬዳዋን የመሠረተ ልማት እና የኮሪደር ልማት ስራዎች ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ በሱፐርቪዥን ለመመልከትና ለመደገፍ እንዲሁም ከሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ጋር ያለውን የአፈፃፀም ልዩነቶች በመለየት ተሞክሮዎችን ለማካፈል ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በጉብኝቱ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

dire tv

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *