“የተጀመሩ ቅንጅታዊ አሰራሮችን አጠናክረን በማስቀጠል በፓርቲያችን የተቀመጡትን አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎችን በስኬት በማጀብ የኢትዮጲያን የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን ልንረባረብ ይገባል”

“ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በተላለፉ ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎች ዙሪያ ያተኮረ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በድሬዳዋ አስተዳደር እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩም የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በአስተዳደራችን ለውጡን ተከትሎ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ለውጡን ዳር ለማድረስ ከጉባኤ እስከ ጉባኤ ነዋሪውን በማንቀሳቀስ ሠላምና ፀጥታ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በማረጋገጥ የፍቅር፣ የወንድማማችነት እና እህትማማችነት ድንቅ ባህላችንን በማጽናት ሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩበት ጠንካራ አስተዳደር በመገንባት፤ ከተማችን ድሬዳዋ ከልማት ኮሪደርነት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የነፃ ንግድ ቀጠና ማዕከልነቷ በተጨማሪ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ ለማድረግ እንደተቻለ ገልፀዋል።

ክቡር ከንቲባ ከድር አያይዘውም የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትን ባህሪ መሠረት ያደረጉ የለውጥ ሥራዎችን በማከናወን ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ከሌብነትና ብልሹ አሰራር የፀዳ ዘመናዊ አገልግሎት በማቅረበ “ዲጂታል ድሬዳዋን” እውን ለማደረግ በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን እየተተገበረ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

የከተማችንን ታሪክና ደረጃ በሚመጥን መልኩ 8 ነጥብ 54 ኪሎ ሜትር በአምስት የተለያዩ አካባቢዎች የደህንነት ካሜራ የተገጠመለት መንገድ፣ ደረጃውን የጠበቀ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የእግረኛና የባይስክል መንገዶች፣ የመኪና ማቆሚያና የስፖርት አካዳሚ ግንባታ እንዲሁም የአረንጓዴ ልማት እና መሰል ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን ያካተተ፤ የኮሪደር ልማት በማከናወን “ስማርት ሲቲ” ለማድረግ በከፍተኛ ርብርብ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም ከንቲባ ከድር አመላክተዋል።

በተጨማሪ የግብርና ምርታማነትን ለማረጋገጥ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት፣ የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት፣ በክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቱሪዝም እንዲሁም በትምህርትና ጤና የነበሩ ስብራቶችን ለመጠገን ውጤታማ ሥራዎችን በስፋት በማከናወን ፓርቲው ለነዋሪው የገባነውን ቃል በውጤታማነት በመፈጸም ስኬቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ከንቲባ ከድር ጠቁመዋል።

በመጨረሻም ከህዝቡ ጋር የተጀመሩ ቅንጅታዊ አሰራሮችን አጠናክረን በማስቀጠል በፓርቲው የተቀመጡትን የሀገሪቱን የወደፊት እድገት እና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎችን በስኬት በማጀብ የኢትዮጲያ የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን ልንረባረብ ይገባል በማለት ከንቲባ ከድር መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ይሱፍ በበኩላቸው የብልፅግና ፓርቲ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ለውጡን በመምራት የህዝቡን ፍላጎት ከዳር እንዲደርስ ታርካዊ ኃላፊነት በመዉሰድ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተስፋን የጫሩና ህዝባችንን ያነቃቁ ስኬታማ ተግባራት እንዳከናወነ ተናግረዋል።

አቶ ኢብራሂም አያይዘውም ከለውጥ አመራሩ ማግስት በአስተዳዳሩ የሚስተዋሉ ችግሮችን እና ነዋሪው በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በጥናት በመመለስ በተለይም ከአጎራባች ክልሎች ጋር በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ፣ በሠላም፣ ፀጥታ እና መሠረተ-ልማት የተጠናከረ ትስስርን በመፍጠር በጋራ የማደግና የመበልጸግ ህልማችንን ዕውን እያደረግን እንገኛለን ሲሉም ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም አቶ ኢብራሂም ከጉባኤ እስከ ጉባኤ ያስመዘገብናቸውን ትውልድ ተሸጋሪ ስኬቶቻችንን በማጽናት እንዲሁም የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በቁጭት እና ቁርጠኝነት ታግለን በመሻገር የጋራ ትርክት የበላይነትንና ቅቡልነትን በማረጋገጥ የተቀመጡ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች በታለመላቸው ደረጃ ለመፈጸም መረባረብ ይገባናል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኤደን ሳሙኤል

ፎቶ፤-አገኘሁ ሸዋረጋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *