ሁለተኛ ቀኑን የያዘው የብልፅግና ፓርቲ የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የ6 ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ እንደቀጠለ ነው።
በመድረኩም የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ የብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅሕፈት ቤት የዘርፍ አመራሮች፣ የክልል ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም የክልል የአደረጃጀት እና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በአጠቃላይ ሀገራዊ ፓለቲካ ሁኔታ፣ ጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ለማሳካትና በፓርቲና በመንግሥት ቅንጅት የሚሰሩ የንቅናቄ አጀንዳዎችን የሚገመግመው መድረክ ዛሬም ቀጥሎ እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ መሰረትም የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ በየደረጃው የተደረጉ ውይይቶች አፈጻጸም በተመለከተ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ ከፓርቲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በፓርቲና በመንግሥት ቅንጅት የሚሰሩ የንቅናቄ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ የሚደረግ ሲሆን በስራ እድል ፈጠራ፣ ከኑሮ ውድነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የሚከናወኑ ስራዎች እና ከተረጂነት ለመላቀቅ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ላይ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ይጠበቃል።
EBC


