በትልልቅ ሀገራዊ የልማት ስራዎች ላይ የተሰራው የተግባቦት ስራ በሰላም ግንባታ ላይም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት “ውጤታማ ተግባቦት ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ሀሳብ ከሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
በውይይት መድረኩ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ፣ በግማሽ ዓመቱ በዋና ዋና መንግስታዊ ጉዳዮች ላይ አጀንዳ የማስጨበጥ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች መተከላቸውን እንዲሁም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ቤቶች መታደሳቸውን እና መገንባታቸውን የሚያሳዩ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ በህዝቡ ዘንድ ግንዛቤ እንዲኖር የሚያስችል ተግባር መከናወኑን ገልጸው፤ በርካታ ሀገራዊ ሁነቶች መከናወናቸውን አንስተዋል።
በሰላም ግንባታ ዙሪያ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አሁንም ግን ሰላምን የሚያውኩ፣ ጥላቻንና ግጭትን የሚቀሰቅሱ መረጃዎች እየተሰራጩ ስለመሆናቸው ነው የገለጹት።
በመሆኑም ብሔራዊ ትርክትን ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስገነዘቡት።
በውይይቱ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሁነቱ አለነህን ጨምሮ የተለያዩ የሚዲያ ኃላፊዎች፣ የክልል የኮሚኒኬሽን አመራሮች እና ባለሙያውች እየተሳተፉ ይገኛሉ።


