በድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በጀርባ ሰፈር የተገነባው የገበያ ማዕከል የእጣ አወጣጥ ስነ-ስርአት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
በዚህም በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር እጣ የማውጣት ስነ ስርአቱ ግልፅና ፍትሀዊ በሆነ መልኩ መከናወኑን ገልፀው፤ 69 ሰዎች እጣ እንዲያወጡ ተደርጎ 29 እድለኞችም እጣ እንደወጣላቸው ተናግረው።
እጣ ያሎጣላቸው ቀሪዎችም በቀጣይ እየተገነቡ በሚገኙ ቤቶች ላይ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አቶ አብዲ አመላክተዋል።
አቶ አብዲ ሙክታር አያይዘውም የዛሬ እጣ የወጣላቸው ባለድለኞች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ መግባት እንደሚገባቸው ያሳሰቡ ሲሆን የገበያ ማዕከሉ በአስተዳደሩ የሚታየውን የመሸጫና የማምረቻ ማዕከልን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለውም አብራርተዋል።
በእጣ ለእድለኞች የወጡት 29 ሱቆች የአስተዳደሩ ክላስተር ልማት ኮርፖሬሽን በባለቤትነት በመረከብም ሱቆቹ ለታለመላቸው አላማ መዋላቸውን እንደሚቆጣጠር ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።
የገበያ ማዕሉ መሰረተ ልማት እንዲሁም ለመሸጫና ለማምረቻ የሚሆኑ ሱቆች የተሟሉበት ሲሆን ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የወጣበት ህንፃ መሆኑንም ተገልጿል።
እጣ የወጣላቸው እድለኞች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በኪራይ ቤት በመቀያየር ይንገላቱ እንደነበረ አንስተው ዛሬ እጣ ስለወጣላቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል፤ በፍጥነትም በሱቃቸው ውስጥ ስራቸውን እንደሚጀምሩ አመላክተዋል።
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ:-አገኘሁ ሸዋረጋ


