የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ
#DGC መጋቢት 26/2017
“ኢትዮጵያ ትችላለች” በሚል መሪ ቃል የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከድሬዳዋ አስተዳደር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 14ኛ አመት በዓል የሚዘክር የውይይት መድረክ አካሄደ።
በዚህም በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ይህ ቀን የሚከበረው ሀገራችን ኢትዮጲያ በመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ለተበሰረው እና ለሰባተኛ ዓመቱ ለበቃው የለውጡ መንግስት ምስረታ ቀንን ምክንያት በማድረግ “የመጋቢታውያን የለውጥ ፍሬዎችና የነገ ተስፋዎች” በሚል መሪ ቃል ባከበረችው በዓል ማግስት መሆኑ ይህንን ቀን ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ምክትል ከንቲባ ሀርቢ አያይዘውም ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት አራቱ ተርባይኖች ሀይል አመንጭተው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ወራቶች መቆጠሩን ጠቅሰው፤ ቀሪ ተርባይኖችም ተመሳሳይ ተግባራቸውን በቅርብ እንዲጀምሩ ርብርብ በመደረግ ላይ ይገኛል ሲሉ ገልፀዋል።
የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያዉያንን በአንድ አስተሳስሮ ወደ ልማት ያስገባና ወሳኝ የኢኮኖሚ ሴንተር እንቅስቃሴ መሆኑ በተፋጠነ ርብርብ አጠናቆ በሙሉ አቅሙ ስራ እንዲጀምር ርብርብ ማድረግ ይገባል ሲሉም ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ተናግረዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ ግንባታዉ በርካታ ፈተናዎችን ቢያስተናግድም አሁን ላይ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልፀው፤ በተለይ ባለፉት የለዉጥ አመታት የተደረጉ ማሻሻያዎች ግንባታዉ እንዲፋጠን እና ለፍጻሜ እንዲበቃ እንዳደረገው ተናግረዋል።
የድሬደዋ ዩኒቨርስቲ የምርምር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል የዛሬው መድረክ ዋና አላማ ለ ፕሮጀክቱ አሁናዊ ስኬት እንደ ህዝብ የከፈልነዉን መስዋእት እስክ ፕሮጀከቱ ፍጻሜ ድረስ ለማስቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ለማሳየት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ በግድቡ ዙሪያ ግንዛቤን የሚያስጨበጡ በርካታ ፕሮግራሞችን ሲያካሂድ የቆየ ከመሆኑ በተጨማሪ በመጀመሪያ ዙር የቦንድ ሽያጭወቅት የ1.5 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዢ የፈጸመ መሆኑን ዶ/ር ተማም ጠቅሰው በቀጣይም ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ አጋርነቱ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የአስተዳደሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የህዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሀብታሙ አሰፋ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 98 በመቶ መጠናቀቁን በመግለፅ ስለግድቡ አጠቃላይ አሁናዊ ገፅታ ማብራሪያ ሰተዋል፤ ቀሪ ስራዎች ሰፊ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቁ በመሆናቸዉ ሁሉም ማህበረሰብ የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከጅምሩ ጀምሮ እስካሁን ያላሰለሰ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተው ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ፤-አገኘሁ ሸዋአረጋ


