የድሬዳዋ ልማት ማህበር የሚያስገነባውን የባለ ሰባት ወለል ህንጻ ግንባታ እና የሚያከናውናቸውን የልማት ስራዎች እስመልክቶ ከድሬዳዋ የሆቴል ባለቤቶችና ስራ አስኪያጆች ጋር ተወያየ፡፡

#DGC መጋቢት 27/2017

የድሬዳዋ ልማት ማህበር በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ወደ ስራ ከገባ ወዲህ አበረታች የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን ጠቅሰው በተለየም የልማት ማህበሩ ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው ለማስቻል የሚያስገነባው ሁለገብ ባለ ሰባት ወለል ህንጻ መንግስት የማይሸፍናቸውን የልማት ክፍተቶች በሞሙላት ረገድ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

የልማት ማህበሩን አቅም ለማጎልበት የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች እያደረጉት ያለው ድጋፍ የሚያበረታታ ነው ያሉት አቶ ገበየሁ ነገር ግን የማህበሩን አባላት ቁጥር በሀገር ወስጥና በውጭ ሀገራት የማሳደግ ስራ አሁንም ብዙ ሊሰራበት ይገባል ብለዋል፡፡

ድሬዳዋ ያላትን መልካም ስም እና ተወዳጅነት መሰረት አድርጎ በርካታ ሀብት ማመንጨት የሚቻልባቸው እድሎች መኖራቸውን የገለጹት የደሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ በተለይም ሆቴሎች ከዚህ አንጻር ሊሰሯቸው የሚገቡ ሰፊ ስራዎችን በቀርነት አንስተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተሳተፉት የድሬዳዋ ሆቴሎች ባለቤቶችና ስራ አስኪያጆች በበኩላቸው ለድሬዳዋ ልማት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አውስተው ነገር ግን ከገንዘብ አስዋጾ ባሻገር በሃሳብና በእውቀት አስዋጾ ማድረግ የሚችሉ የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆችንም በመሰል ሁኔታ መድረክ አዘጋጅቶ በገንዘብ የማይተመኑ የሀብት ምነጮችን ማግኘት የሚቻልባቸውን አማራጮችም ማየትና መፈተሽ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ፡፡

በሆቴላቸው የሚስተናገዱ እንግዶቻቸውና ተገልጋይ ደንበኞቻቸው ስለ ልማት ማህበሩ እንዲያውቁ በማድረግ በገንዘብና በሃሳብ የበኩላቸውን አስተዋጾ እንዲያበረክቱ የሚያስችሉ ስራዎችን እንደሚሰሩ የገለጹትየአል ሒላል ሆቴል ባለቤት ወይዘሮ ዘሐራ ሁሴን ፣ እንዲህ ባለው መድረክ ላይ የመወሰን አቅም ያላቸው ባለንብረቶች ቢሳተፉ ውጤታማ ምክክር ማድረግ ያስችላል ያሉ ሲሆን በሆቴላቸው ስም የሁለት መቶ ሺ ብር ስጦታ አበርክተዋል ፡፡

ድሬደዋ ከምናድርግላት ያደረገችልን ይበልጣል ያሉት የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ለድሬዳዋ ልማት ማህበር የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹ ሲሆን የልማት ማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ ከተማ ተሰማ ከሆቴል ባለቤቶች የሚደረገውን ድጋፍ ተሰባስቦ ሲጠናቅቅ ይፋ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል፡፡

በመጨረሻም የድሬዳዋ ልማት ማህበር አባልነት ምዝገባና የአባልነት መታወቂያ በመያዝ ለድሬዳዋ ያለንን ፍቅር በተግባር እናሳይ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዳንኤል አማረ

ፎቶ፡- ሰላም አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *