1446ተኛው ሒጅርያ ሹዋሊድ ክብረ በዓል “የአንድነት፣ የሰላም፣ የልማትና የብልፅግና ተምሳሌት” በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ በድምቀት ተከብሯል።
በዚህም በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በሀረሪ ብሔረሰብ ልዩ ባህላዊ መገለጫ ለሆነው የሸዋል ዒድ ክብረ በአል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከንቲባ ከድር አያይዘውም በዓሉ ሰላምን፣ ፍቅርንና መቻቻልን የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር ህብረ- ብሄራዊነት ጎልቶ የሚታይባት በርካቶች ባህልና እምነታቸውን በመከባበር፣ በፍቅርና በጋራ የሚጋሩበት ና በድምቀት የሚያከብሩባት እንደሆነ ከንቲባ ከድር ተናግረው ይህ በዓልም በትንሿ ኢትዮጲያ ድሬዳዋ በመከበሩ የተሰማቸውን ደስታ ተናግረዋል።
ክቡር ከንቲባ ከድር አያይዘውም በአሉ በድሬዳዋ ከወንድም ብሄር ብሄረሰቦችና የተለያዩ ነዋሪዎች ጋር በደመቀ መልኩ በጥምረት መከበሩ የህዝቦችን የጋራ አንድነት ለማጠናከር፣ ለባህል ትውውቅና ልውውጥ ለዜጎች መቀራረብ ፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርና ግንኙነትን ለማጎልበት ከፍተኛ ሚና እንዳለው አብራርተዋው፤ ይህም ለአስተዳደሩ የቱሪዝም ዘርፍ መጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ከንቲባ ከድር ጠቁመዋል።
የድሬዳዋ የሀረሪ ኮሚቴ ተወካይ ፈቲያ አብዱልከሪም በበኩላቸው የሸዋሊድ ክብረ በአል በሁሉም ሀረሪ ማህበረሰብ ዘንድ በከፍተኛ ጉጉትና ድምቀት በተለያዩ ባህላዊ ስነ-ስርአቶች በአብሮነት ስሜት የሚከበር መሆንን አንስተው፤ ወጣቶችም የወደፊት የህይወት አጋራቸውን የሚመርጡበት በዓል መሆኑን አብራርተዋል።
ዘንድሮም በዓሉ በድሬዳዋ በመከበሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ለፕሮግራሙ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋፆ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ:-ሰላም አበበ


