በድሬዳዋ አስተዳደር ከፍልሰት ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም በኢኮኖሚ ውጤታማ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ለባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በዛሬው እለት ተካሂዷል ።
በዚሁ መርሀ-ግብር ላይም በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ\ሮ ሁክሚያ መሀመድ አምራች ሀይል የሆኑት ወጣቶች ተደራጀተው የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ከራሳቸውም አልፈው ሀገራቸውን መለወጥ እንዳለባቸው ተናግረው ወጣቶች በሀገር ላይ ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉም የተናገሩት ።
ለአንድ ወጣት 32 ሺህ ብር 10 ወጣቶች ሆነው በማህበር ለሚደራጁ ማህበራትም 320 ሺህ ብር በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረጉ ስራ እንደሚሰራ በድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ጉዳይ ኤጀንሲ ስራ አስከያጅ አቶ አብዱረህማን ሙሳ ተናግረው 160 ለሚሆኑ ወጣቶች ከሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ አስፈላጊውን የሙያ ድጋፍ እንደሚሰጣቸውም ነው አቶ አብዱረህማን ያስታወቁት ።
ወጣቶች የራሳቸውን ስራ ሰርተው የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ሴቭ ዘ ቺልድረን ባለፍት አመታት በርካታ ስራዎች መስራቱን የሴቭ ዘ ቺልድረን አስተባባሪ አቶ ሀጂ መሀሙድ ኡስማኤል ተናግረው ወጣቶች በስራ እራሳቸውን እንዲለውጡ ከሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ ባሻገር የተለያዩ ስልጠናዎች እንደሚሰጡም ነው የተናገሩት ።
በአለማየሁ አበበ
ፎቶ:- ሰላም አበበ


