በኢፌድሪ አየር ሀይል የሶስተኛ አየር ምድብ የሰራዊት አባላትና አመራሮች በዛሬው ዕለት በክብር ዶ/ር አሰገደች አሰፋ የአረጋዊያን መጦሪያ ማዕከል በመገኘት ማዕድ አጋርተዋል።
በመርሀ ግብሩ የተገኙት የኢፌድሪ አየር ኃይል የ3ኛ አየር ምድብ ዋና አዛዥ ኮ/ል ደረጀ ቡሽሬ የዛሬው ፕሮግራም በዋነኝነት ለሀገራችን በርካታ ቁም-ነገሮችን ላበረከቱ እናት አባት አረጋውያን ያለንን ለማካፈልና ለዳግማ ትንሳኤ በዓል ማዕድ በማጋራት እንኳን አደረሳችሁ ለማለት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኮ/ል ደረጀ አያይዘውም ሀገራችንን በጀግንነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን አቅመ ደካማ ወገኖቻችንን በመጎብኘት ከጎናቸው መሆናችንን ማሳየት ይገባናል ያሉ ሲሆን ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የክብር ዶ/ር አሰገደች አሰፋ ልጅ ወ/ሮ እመቤት መኮንን በበኩላቸው ለተበረከተው የአስቤዛ ድጋፍ በማመስገን የኢፌድሪ አየር ሀይል የሶስተኛ አየር ምድብ ሰራዊት አባላት ከአረጋውያን ጎን በመቆም በርካታ ድጋፍ እያበረከቱ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ድጋፉ የተደረገላቸው አረጋዊያን በበኩላቸው በተበረከተው ስጦታ መደሰታቸውን ገልፀው፤ በዓልን ስናከብር ያለው ለሌለው በማካፈል እንዲሁም አረጋዊያንን በመጎብኘት ሊሆን ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ:- አገኘሁ ሸዋረጋ


