በዛሬው ዕለት በሐረሪ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት የተመራ ልዑካን ቡድን የድሬዳዋ የመጀመሪያ ደረጃና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፉና ዲጂታላይዝ በማድረጉ ረገድ የሰሯቸውን ስራች ጎብኝተዋል፡፡
ልዑክ ቡድኑ በጉብኝቱ የአንድ መስኮት አገልግሎትንና የስማርት ኮርት ሩም ስራዎችን ተዘዋውሮ የተመለከተ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቶቹ በዳኝነት ዲጂታላይዜሽንና በሪፎርም ስራ ያከናወኑአቸው ስራዎች ላይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ውይይት አድርጓል፡፡
የዛሬው መድረክ የልምድ ልውውጥ መሆኑን በመግለፅ ፍርድ ቤቶች ተገልጋዮች የሚበዙበት በመሆኑ በተቀላጠፈ መልኩ አገልግሎት ለመስጠትና ከማህበረሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ቅሬታዎችን በአፋጣኝ ለመፍታት የስራ ቦታን ምቹና ዘመናዊ ማድረግ ጉልህ ሚና እንዳለው የተናገሩት የድሬዳዋ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የተከበሩ አቶ አብዲ መሀመድ በፍርድ ቤቶቹ በአንድ መስኮት አገልግሎት ስራ መጀመሩ ተገልጋዮች ጉዳያቸውን ሳይንገላቱ እንዲሁም ጊዜያቸውን ቆጥበው እንዲጨርሱ እንዳስቻላቸው አብራርተዋል፡፡
የሐረሪ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት የተከበሩ አቶ ማሂር አብዱሰመድ በበኩላቸው የድሬዳዋ የመጀመሪያ ደረጃና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ለባለጉዳዮች የአንድ መስኮት አገልግሎት በመስጠትና አሰራርን ዲጂታላይ በማድረጉ ረገድ አበረታች ስራዎች እየሰሩ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡
በስራ ሂደት ላይ የሚገኙት የእስማርት ኮርት ሩምም ዘመናዊ በሆነ መልኩ ግንባታቸው እየተከናወነ እንደሚገኝ መመልከታቸውን አቶ ማሂር ተናግረው፤ ፍርድ ቤቶቹ እየተጠቀመባቸው የሚገኙ መተግበሪያዎችና የ ኢ-ፋይሊንግ አሰራሮችም የተገልጋይን ጊዜ ቆያቢ እንዲሁም የፍርድ ቤት ገለልተኛነትን የሚያሳዩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የእስካይ ሊንክ ቴክኖሎጂ መስራችና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አህመድከረም አህመድ እንግዶቹ በቆይታቸው በአጠቃላይ የእስማርት ኮርት ፕሮጀክት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ እንደጎበኙ በመጠቆም፤ ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤቶቹ በማንዋል ያከናውኑ የነበረውን ስራ አሁን ላይ ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራ መሰራቱን በዚህም የአንድ መስኮት አገልግሎትን እስማርት በሆነ መንገድ በሶስት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተሰርቶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡
አቶ አህመድከረም አያይዘውም በስራ ሂደት ላይ የሚገኙት የእስማርት ኮርት ሩም ስራዎችም በአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ውስጥ እንደሚጠናቀቁ ጠቁመዋል፡፡
ሁለቱ የድሬዳዋ አስተዳደር የመጀመሪያና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች በጋራ በመሆን የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ ስራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑት አቶ አብዱለዚዝ ሻፊ ናቸው፡፡ አቶ አብዱለዚዝ በቀጣይ ተገልጋይ የሚበዛበትን ተቋም ዲጅታላይዝ የማድረግ ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ፡-ሰላም አበበ


