አፍታሜይራ ግሩፕ ኢምፖርት ኤክስፖርትን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶችን የሚያስተዳድር ሲሆን በአዲስ አበባም የተለያዩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየሰራ ይገኛል ።
በድሬዳዋ አስተዳደርም የ 20 \ 80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችለውን ስምምነት በዛሬው እለት ከድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ጋር ተፈራርሟል ።
አፍታሜይራ ግሩፕ ድሬዳዋ ላይ የሚያስገነባቸው ቤቶች በመሀል ከተማዋ ላይ ከመሆኑም በላይ የቤት ባለቤት ለመሆን ቅድሚያ 20 ፐርሰንት ቀሪውን 80 ፐርሰንት ደግሞ በ 15 አመት ውስጥ መክፈል እንደሚችሉ የአፍታሜይራ ግሩፕ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አሚር አብዱልዋሀብ የገለፁ ሲሆን የቤቶቹ ግንባታዎችም ከ ዘጠኝ ወር እስከ አንድ አመት ባለው ጊዜ ውስጥም እንደሚጠናቀቁም ነው ያስታወቁት ።
አቶ አሚር አክለውም በያዝነው አመት እስከ አንድ ሺህ የሚሆኑ ቤቶች ለመገንባት እቅድ እንዳላቸው ያስታወቁ ሲሆን ቤቶቹ በሚገነቡበት አካባቢ ይኖሩ ለነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችም የሚገነቡት ቤቶች እንደተጠናቀቁም ለተነሺዎቹ ምትክ ቤት እንደሚሰጣቸው ነው አቶ አሚር ያስታወቁት ።
የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ በድሬዳዋ አስተዳደር በከተማም ሆነ በገጠር ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ተሾመ አበበ ተናግረው በተለይም ቤት ለመግዛት በአንድ ጊዜ መክፈል ለማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ቅድመ ክፍያ 20 ፐርሰንት ከፍለው ቀሪውን 80 ፐርሰት በረጅም ጊዜ ክፍያ ከፍለው ማጠናቀቅ እንደሚችሉ ተናግረው ቤት ፈላጊዎች በ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ከ 50 ብር አንስተው መቆጠብ እንደሚችሉም ነው የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ተሾመ አበበ የተናገሩት።
በአለማየሁ አበበ
ፎቶ :- በአገኘው ሸዋረጋ


