“የጤና ባለሞያው በበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ መርሀ ግብር ላይ መሳተፉ ለሌሎች የሀገሪቷ ክፍል ጤና ባለሞያዎችም መልካም ተሞክሮ የሚሆን ነው።” – አቶ ዩሱፍ ሰኢድ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ

#DGC ግንቦት 04/2017

“በወሊድ ወቅት በሚከሰት የደም እጥረት ምክንያት የሚከሰትን የእናቶች ሞት ለመታደግ ደማችንን እንለግሳለን” በሚል መሪ ሀሳብ በድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ስር ያሉ የጤና ተቋማት ጤና ባለሞያዎች የበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ መርሀ ግብር አካሄዱ።

የጤና ባለሞያዎቹ በወሊድ ምክንያት በሚፈጠር የደም እጦትና ሌሎች አደጋዎች የአንዲትም እናት እንዲሁም ነዋሪው ለህልፈተ ህይወት እንዳይዳረግ ደማቸውን በመለገስ ወገናዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በተማሩበት የሞያ መስክ ለማህበረሰቡ ከሚሰጡት ሞያዊ አገልግሎት ባሻገር በተለያዩ ግዜያት በጤና ተቋማት በደም እጦት ምክንያት የሚከሰተውን ህልፈተ ህይወት ለመቅረፍ በደም ልገሳ የበጎ ፍቃድ ማህበራዊ አገልግሎት ላይ በመሳተፍ ማህበረሰቡን ማገልገል በመቻላቸው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን በበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ መርሀ ግብሩ ላይ ያነጋገርናቸው የጤና ባለሞያዎች ገልፀውልናል።

በደም ልገሳ መርሀ ግብሩ ተገኝተው ደም ለጋሽ ጤና ባለሞያዎችን ያበረታቱት የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል አስተባባሪነት ከተለያዩ ጤና ተቋማት ተውጣተው በበጎ ፍቃድ ደም ለለገሱ የጤና ባለሞያዎች ምስጋናቸውን የቸሩና በጤና ባለሞያዎቹ የተከናወነው የበጎ ፍቃድ ደም ልገሳ የጤና ባለሞያዎቹ ለሚያገለግሉት ህብረተሰብ ያላቸውን ተቆርቋሪነት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተነሳ ያለውን የጤና ባለሞያዎች የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄን የድሬዳዋ ጤና ባለሞያዎችም በሰላማዊ መንገድና ህብረተሰባቸውን እንዲህ ባለው የበጎ ፍቃድ የደም ልገሳ በማድረግም ጭምር መንግስት የሚሰጣቸውን ምላሽ መጠበቃቸው በሌሎችም የሀገራችን ክፍል ላሉ የጤና ባለሞያዎች መልካም ተሞክሮ ከመሆኑም ባሻገር ቢሮውም ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው አካል ማስተላለፉን ተናግረው የጤና ባለሞያዎችን አመስግነዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *