ግብርን በታማኝነት መክፈል የሀገር ወዳድነት ምልክት መሆኑ ተጠቆመ

የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የአገርን እድገት ለማስቀጠል ግብር ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሲሆን፤ ይህንን በመረዳት በድሬዳዋ አስተዳደር በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ግብራቸውን በታማኝነትና በግንበር ቀደም የሚከፍሉ ግብር ከፋዮች ግብርን በታማኝነት መክፈል የሀገር ወዳድነት ምልክት ነው ሲሉ ይናገራሉ።

በዚህም የቢኒያም ብረታ ብረትና የህንፃ መሳሪያ መሸጫ ባለቤት የሆነው ወጣት ቢኒያም ይትባረክ ግብሬን በአግባቡ በመክፈል በተደጋጋሚ ተሸላሚ ሆኛለሁ በዚህም ኩራት ይሰማኛል በማለት የተናገረ ሲሆን፤ የግብር ዋነኛ ግብ የዜጎችን የመሰረተ-ልማት ፍላጎት ምላሽ በመስጠት የአገርን ኢኮኖሚ ማሳደግ መሆኑን ገልጿል።

በኮንስትራክሽን የስራ ዘርፍ ላይ የተሰማራው የመላኩ ተስፋዬ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ኢንጂነር መላኩ ተስፋዬም በተደጋጋሚ ግብርን በታማኝነትና በግንባር ቀደምነት በመክፈል ተሸላሚ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ ይላሉ።

ኢንጂነር መላኩ አያይዘውም ሁሉም ማህበረሰብ ግብሩን በአግባቡ በመክፈል ለሀገሩ ልማት የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ግብርን በታማኝነት መክፈል የአገርን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣትና ልማትን ለመደገፍ ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው የተናገሩት ደግሞ የኬር እስኩየር ሆቴል ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዘነበ አበበ ናቸው፤ አቶ ዘነበ አያይዘውም ለረጅም ጊዜያት ግብራቸውን በጊዜና በታማኝነት ሲከፍሉ መቆየታቸውን ገልፀው ይህ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *