ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት በመከተል የወደፊት ፍላጎታችንን ለማሳካት እየሰራን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በ2ኛው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ስትራቴጂና ፖሊሲዎችን ቀርፃ ተግባራዊ እያደረገች ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው የተመድ የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በኋላ፣ ከሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር የተጣጣመ አካታች የምግብ ሥርዓት ሽግግር ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ተግባራዊ ማድረጓንም አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አያይዘውም ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ ሽግግር በማድረግ በተግባር ውጤት ማየት ጀምረናል ብለዋል፡፡
አክለውም በሰቆጣ ቃል ኪዳን፣ በሌማት ትሩፋ እና ሌሎችም ውጥኖች የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቋቋም እንዲሁም የስራ እድልን በመፍጠር እየተከናወነ ያለውን ስራ እና የተገኘውን ለውጥ ጠቅሰዋል።
እንደ ሀገር ሰው ተኮርና የተቀናጀ መንገድ በመከተል፣ በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ነው የጠቀሱት፡፡
በሀገር ውስጥ የምግብ የማምረት አቅምን ለማሳደግ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እየተደረገ መሆኑን አንስተው፣ ይህም ሀገሪቱን ከውጭ ጥገኝነት ማለቀቅ አስችሏታል ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አፍሪካ ከማንም ሳትጠብቅ ራሷን የመመገብ አቅም እንዳላት ገልጸው፣ ይህን እውን ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻዎች በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።


