ዓለም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በአንድነት የሚቆምበት ጊዜው አሁን ነው፦ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ

ዓለም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በአንድነት የሚቆምበት ጊዜው አሁን ነው ሲሉ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ገለፁ።

ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በመካሄድ ላይ ባለው 2ኛው የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ሥርዓታችን አሁን ከመቼውም በላይ በፈተና ውስጥ ያለ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ አካታች የሆነ የምግብ ሥርዓት ለማረጋገጥ በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል።

በሶማሊያ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ተደራራቢ ማህበራዊ ቀውሶች ህዝባችንን ለመመገብ የምናደርገውን ጥረት አዳጋች አድርጎታል ነው ያሉት።

ሀገሪቱ እየተገበረችው ባለው ብሔራዊ የሽግግር ዕቅድ ግብርናን ቁልፍ መሳሪያ በማድረግ አካታች የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።

ከግብርና አኳያ ምርታማነትን ማሳደግ፣ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት፣ አግሪ ቢዝነስን ማጠናከርና ተቋማትን መገንባት ዋነኛ ትኩረት ስለመሆናቸው ዘርዝረዋል።

በተጨማሪም ሀገሪቱ የማይበገር የምግብ ሥርዓት እውን ለማድረግና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗን ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት።

#EBC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *