ሴንተር ፎር ሪስፖንሲብል ኤንድ ፒስፉን ፖለቲክስ ከሂራድ ፐብሊክ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ጋር በመቀናጀት ያዘጋጁት “የመገናኛ ብዙሀን እና የጋዜጠኞቾ ሚና በግጭት መከላከል እና ሰላም ግንባታ በዲጂታል ዘመን” በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ በሱማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህም በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ መሀሙድ በተለያዩ አለመግባባቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማረጋጋት ሚዲያ ያለው አቅም ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ ሚዲያን ለልማትና ለበጎ ዓላማ መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል።
መገናኛ ብዙሀንና ጋዜጠኞች በተለይም በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚዘዋወሩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በመከላከል ትክክለኛ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ በፍጥነት ማድረሱ ላይ ተቀናጅቶ መስራት ይገባቸዋል ሲሉ ፕሬዝዳንት ሙሰጠፌ ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሀንን በመጠቀም የጋራ ትርክትን መገንባት ኢትዮጵያ ወደ ፊት ለምታደርገው ጉዞ ወሳኝ እርምጃ በመሆን የሀገርን አንድነት እንደሚያሰፍንም በመድረኩ ተጠቁሟል።
መድረኩ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ መሀሙድ፣ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፣ አምባሳደር መሃሙድ ድሪሪ፣ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ፣ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች እየተሳተፉም ይገኛሉ።


