ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ስታስተናግድ እንደ መሰብሰቢያ ብቻ ሳይሆን ሁሉን አካታች በሆነው መደመር ያሳካቻቸውን ግቦች እና ዓላማዋን ለማጋራት ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ተሳታፊዎች በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የእራት ግብዣ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእራት ግብዣው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “የተሰባሰብነው ራት ለመብላት ነው፤ በጣም አስፈላጊው ጉዳይ በጋራ ማዕድ ዙሪያ የምንጋራው ሀሳብ ነው” በማለት የመሰባሰቡን ዓላማ ገልጸዋል።
ጉባኤውን አስመልክተውም ምግብ ዝም ብሎ ሸቀጥ ሳይሆን ትውስታ፣ መለያ፣ ሉዓላዊነት እና የመኖር ዋስትና መሆኑን ጠቅሰዋል።
“በዐፈራችን ላይ የምንዘራው በሥርዓታችን ልንይዝ የሚገባንን እሴት የሚገልጽ ነው” በማለት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
እነዚህ እሴቶችም ጥንካሬ፣ ፍትሃዊነት እና መተማመን እንደሆኑ ጠቅሰው፤ የሀገራት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በጉባኤው ሲታደሙ ለማኅበረሰቦች እና ለአርሶ አደሮች የሚሆን ራዕይ ሰንቀው ሊሆን እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።
በምግብ ራስን ለመቻል በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ዲጂታል ቴክኖሎጂን ከነባር ዕውቀት ጋር ማሰናሰል እንዲሁም ስማርት ግብርና እና አካታችነትን እውን ማድረግ ከተቻለ ዓላማውን ማሳካት እንደሚቻል ገልጸዋል።
ይህን ለማሳካት ግን ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን ትብብር፣ ፈጠራ እና ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእራት ግብዣ ስለተደረገበተ ቤተ-መንግሥት ሲገልጹም፥ እስከ ቅርብ ጊዜ ከሕዝብ ተደብቆ የቆየው ቤተ-መንግሥት ደረጃውን በሚመጥን መልኩ መታደሱን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያን ጥንታዊ እና ታላቅ ታሪክ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።


