አካባቢን በማልማት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አለመቻል ተስፋ መቁረጥን በመፍጠር ወደ ግጭት፣ ሽብርተኝነት እና ፍልሰት የሚያመራ የዓለም ስጋት መሆኑን የጣሊያን ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሚኒስትሮች ምክርቤት ፕሬዚዳንት ጆርጂያ ሜሎኒ ገለጹ።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ሁለተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ሥርዓት ጉባዔ ላይ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፥ ጉባኤው በአፍሪካ ሲካሄድ የመጀመሪያው መሆኑን ጠቅሰው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ላደረጉት መስተንግዶ አመስግነዋል።
ጣሊያን ጉባኤውን ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን ለማዘጋጀት የወሰነችው ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት ስላላት ብቻ ሳይሆን በወሳኝ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ድምጿ ያነሰውን አፍሪካን በጉዳዩ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንድትሆን በማሰብ እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ ገልጸዋል።
የጉባኤው አስፈላጊነት በዓለም ላይ ፈተና የሆነውን የምግብ ዋስትና ችግርን ለመፍታት የጋራ አቋም ለመያዝ እና ትብብርን ለማጠናከር እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የምግብ ዋስትና ባለፉት 70 ዓመታት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፤ 10 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ክፍል በዚህ ረገድ በከፋ ችግር ውስጥ መሆኑን አስታውሰዋል።
የምግብ ዋስትና ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ያለበት የዓለማችን ክፍል በሆነው አፍሪካ ከ5 ሰዎች አንዱ አስከፊ የምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ ያለ በመሆኑ ብዙ ትኩረት እንደሚፈልግ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህን አሳሳቢ ችግር በፍጥነት ለመቅረፍ የሩስያ-ዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ ዓለም አሁን ያለችበት ውስብስብ ሁኔታ ፈተና መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሯ ያወሱት።
ዓለም በገጠማት ፈተና ምክንያት የደቡብ የዓለም ክፍልን እና አፍሪካን ያጋጠመውን የኃይል እጥረት እና የምግብ ሸቀጦች ዋጋ መናርን ለመፍታት በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የምግብ ዋስትና የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለንን አቅም ከቆጠብን እና ችላ ካልን ዓለምን ወደ ከፋ ቀውስ የሚያመራ ታሪካዊ ስህተት እንሠራለን ብለዋል።
የምግብ ሥርዓት የተሻለ ምጣኔ ሀብት ላላቸውም ሆነ የድህነት ቀውስ ውስጥ ላሉ ሀገራት በእኩል ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፤ ጉዳዩ የሁሉም የትኩረት መስክ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
የምግብ ዋስትናን በተሟላ ሁኔታ ለማረጋገጥ የቤተሰብ ፍጆታን ከማሟላት ባለፈ ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ትርፍ አምራችነትን ማበረታታት እና የሥራ ዕድልን በመፍጠር የተረጋጋ ማኅበረሰብን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ጣሊያን በዘመናዊ ግብርና የዳበረ ልምድ እንዳላት ያወሰቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ፤ ሀገራቸው ይህን ልምድ ለአፍሪካ በማጋራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ እንደምትሠራ ገልጸዋል።
በዚህም ጣሊያን በአፍሪካ ባለድርሻዎችን እንዲሁም የመንግሥት እና የግል ባለሀብቶችን ጥምረት በማጠናከር እየሠራች መሆኗን ጠቁመዋል።
በአልጄሪያ በረሃ 36 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 44 ሺህ ቶን ምርት ለማግኘት እየተሠራ ያለው ሥራ ለዚህ ትብብር አብነት መሆኑን ገልጸዋል።
ተመሳሳይ ሥራ በሴኔጋል፣ ጋና እና ኮንጎ እተሠራ መሆኑን እንዲሁም በኬንያ እና ኮትዲቯር እንደሚተገበር፣ በቱኒዚያም ልምዱን የማካፈል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጣሊያን አፍሪካን የምትደግፈው ጥገኝነትን ለማበረታታት ሳይሆን፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ራስን የመቻል መንገድን ለማሳየት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ።


