የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በ2ኛው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባዔ በበይነ መረብ ለታዳሚዎች ባስተላለፉት መልዕለክት፤ ሀገራት ለብዝኀ ሕይወት እና ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት በመስጠት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ጣሊያን ከተመድ ጋር በመተባበር 2ኛውን የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በጋራ በማዘጋጀታቸው ዋና ጸሐፊው አመስግነዋል፡፡
ሀገራት በመደበኛ በጀታቸው ውስጥ ለአካባቢ ጥበቃ እና የብዝኀ ሕይወት እንክብካቤ ተጨማሪ በጀት በመያዝ የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ መስራት እንዳለባቸው በመልዕክታቸው ገልጸዋል፡፡
በዚህ ጊዜ ደግሞ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ አሰራሮችን ለአርሶ አደሮች ማድረስ ያስፈልጋል ብለዋል።
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የመንግሥታት ስራ ብቻ ሳይሆን የግሉ ዘርፍም ሊሰማራበት ይገባል ያሉት ጉተሬዝ፤ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች በሚንቀሳቀስበት የምግብ ዘርፍ ተሳታፊ በመሆን ራሳቸውን በኢኮኖሚ፣ ሕዝባቸውን ደግሞ የምግብ ዋስትናን እንዲያረጋግጥ ማድረግ ይችላሉ ሲሉ ገልጸዋል።
ደህንነቱ እና ጥራቱ የተጠበቀ ምግብ ለሁለም መዳረስ እንዳለበት ገልጸው፤ ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ አለባቸው ነው ያሉት፡፡
በዓለም ዙሪያ በምግብ አያያዝ ችግር ብቻ በዓመት በትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ምግብ ይባክናል፤ ይሕን ማስተካከል ይኖርብናል ብለዋል አንቶኒዮ ጉቴሬዝ።
ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተመሰረተ የምግብ ጥገኝነትን በማስቀረት ራስን ለመቻል ሀገራት ለአየር ንብረት ተስማሚ የምግብ ፖሊሲ ሊተገብሩና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ሊያሳድጉ እንደሚገባ ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል፡፡


