በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በተፃፈው በመደመር ትውልድ መፅሀፍ ሽያጭ እንዲሁም በአስተዳደሩ ድጋፍ ዘመናዊና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተገነባው እመርታ ቤተ-መፅሀፍ አሁን ላይ የግንባታ ሂደቱ እንደተጠናቀቀና በቅርቡ ተመርቆም ለነዋሪዎች ክፍት እንደሚሆንም የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወንደሰን አባይ ተናግረዋል።
ቤተ-መፅሀፉ በአንድ ጊዜ አንድ ሺ የሚሆኑ ተጠቃሚዎችን ማስተናገድ እንደሚችል የጠቆሙት አቶ ወንደሰን አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም ለድሬዳዋ ነዋሪዎች የንባብ ባህል መዳበር ጉል ሚና እንደሚጫወት ገልፀዋል።
በውስጡ የአይሲቲ ሩም፣ ለአካል ጉዳተኛ ወገኖች ምቹ የማንበቢያ ስፍራዎችን፣ ለሙሁራን እና ለተመራማሪዎች የጋራ መወያያ ክፍልን፣ ካፍቴሪያን፣ ደረጃቸውን የጠበቁ መፀዳጃ ቤቶችን፣ ከ40 በላይ መኪናዎችን የሚያስተናግድ የመኪና ማቆሚያ ስፍራን፣ የህፃናት ማቆያ ዴኬርን፣ የሰኪውሪቲ ክፍሎችን እና ሌሎችም መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ ጊቢው ለአንባቢያን በሚማርክ መልኩ ፋውንቴንን እና አረንጓዴ ስፍራዎችን አካቶ መሰራቱን ኃላፊው አብራርተዋል።
ቤተ-መፅሀፉ ስራ ሲጀምር በሶስት ሽፍት 24 ሰዓት እንደሚሰራ አቶ ወንደሰን ተናግረው፤ለቤተ-መፅሀፉ የመፅሀፍት፣ የኮምፒተር እና ሌሎችም መሰል መገልገያ ቁሳቁሶችን ማበርከት ለሚፈልጉ አካላትም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።


