የኑሮ ውድነቱን እና የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት ‘የኢትዮጵያን ይግዙ’ የንግድ ሳምንት ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው ተገለፀ

በድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የተዘጋጀው ሁለተኛው “የኢትዮጲያን ይግዙ” የንግድ ሳምንትን በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ተከፍቷል።

የንግድ ሳምንቱ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚካሄድ የገለፁት የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር ለአምስት ተከታታይ ቀናት ማለትም ከነሀሴ 12 እስከ ነሀሴ 16/2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ አመላክተዋል።

ብዙ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን እና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋወቁበት መሆኑን አቶ አብዲ ጠቅሰው፤ ከ50 በላይ የሚሆኑ የንግድ ድርጅቶች እና ነጋዴዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ እና በተለይም አምራች ኢንደስትሪዎች ከህዝብ ጋር በደንብ የሚተዋወቁበት እንዲሁም ብዙ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን እና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋወቁበት ሳምንት መሆኑን አመላክተዋል።

የአስተዳደሩ ንግድ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሚኖ ጠሃ በበኩላቸው የግብርና ምርቶች፣ የኢንደስትሪ ምርቶች እና በተለይም ከውጪ በአስመጪዎች አማካኝነት የሚመጡ ምርቶች የሚቀርቡበት ኤግዚብሽን እና ባዛር መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ አሚኖ አያይዘውም የንግድ ሳምንቱ የኑሮ ውድነትን እና የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የጠቆሙ ሲሆን የምርት አቅርቦትን ለማመቻቸት በተጨማሪም ፍላጎትን እና አቅርቦትን ለማቀራረብ የሚደረግ ጥረት መሆኑን አብራርተዋል።

ከቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ቀጥሎ በዚህ የንግድ ሳምንት አቅርቦቶችን ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ስራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ አሚኖ ማህበረሰቡም ወደ ገበያው በመምጣት የሚያስፈልገውን እንዲሸምት ጥሪ አቅርበዋል።

“የኢትዮጵያን ይግዙ” 2ኛው ሀገራዊ የንግድ ሳምንት ከነሐሴ 24-29 ቀን 2017 ዓ.ም መገናኛ በሚገኘው በጥራት መንደር ይካሄዳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *