በመርሃ-ግብሩም የ2017 ዓ.ም የሥራ አፈፃፀም እና የኦዲት ሪፖርቶች እንዲሁም የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ፀድቋል።
በመድረኩ የተገኙት በኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮምሽን የፋይናንስ ህብረት ስራ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሀኑ ዱፌራ የኛ ቁጠባ እና ብድር ኅላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ስራ ማህበር ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም አሁን ላይ እያከናወናቸው የሚገኙት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረው፤ በሁለት አመት ውስጥ 3 ሺ የሚጠጋ አባል እንደሰበሰበ እንዲሁም አባላቱም ቁጠባቸውን እየተቆጠቡ ብድር እየተበደሩ ስራቸውን በማገዝ ኢኮኖሚያቸውን እያሳደጉ እንደሆነ ገልፀዋል።
ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተደራጅተው ስራዎችን ለመስራት ሲያስቡ የፋይናንስ ግብአት እንደሚያስፈልግ አቶ ብርሀኑ ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ እንደ የኛ ያሉ አሰራራቸውን ለማህበረሰቡ ምቹ እና ዘመናዊ እያደረጉ የሚገኙ የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ተመራጭ እንደሆኑ አመላክተዋል።
አቶ ብርሀኑ አያይዘውም ተቋሙ የብድር አቅርቦት ላይ ለተጠቃሚዎች በሚመች መልኩ የዋስትና ስርዓት በመዘርጋቱ በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙም ገልፀዋል።
ተቋሙ በ2017 ዓ.ም የአባላት ቁጥርን ለመጨመር እና የፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንደሰራ እና በዚህም የአባላቱ ቁጥር፣ የሚሰበሰበው የቁጠባ መጠን እንዲሁም የተሰጠው የብድር መጠን ማደጉን አቶ ብርሀኑ አመላክተው በአጠቃላይም የብድር አመላለሱም ጤናማ የሚባል መሆኑን አብራርተዋል።
በቀጣይም በ2018 በጀት ዓመት በስፋት ተቋሙን የማስተዋወቅ እና የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ላይ እንደሚሰራ ከመድረኩ የተመላከተ ሲሆን፤ በየጊዜውም ተቋሙ ራሱን እያሳደገና እያዘመነ ለድሬዳዋ ነዋሪዎች ከፍተኛ ጥቅምን የመስጠቱ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከመድረኩ ተመላክቷል።
በመድረኩ ብድር በወቅቱ ለሚከፍሉ እንዲሁም የመደበኛ ቁጠባን በተመሳሳይ በወቅቱ ለሚከፍሉ የእውቅና ሽልማት ተበርክቷል።


