በአስተደደሩ የሚገኙ ተቋማት አመራሮች እና ሰራተኞች ለተገልጋዮች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ቀጣይነት ያለው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ተገለፀ።

በድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ እና በድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይር ሀጂኑር የተመራ ቡድን በአስተዳደሩ የከተማ ወረዳዎች ድንገተኛ ምልከታ አደረገ።

የምልከታው ዋንኛ አላማ በወረዳዎቹ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ነባራዊ ሁኔታ በአካል ተገኝቶ ለመመልከት እና በተለይም የተገልጋይ ቀን ተብለው በሚታወቁት እለተ ሰኞ እና ረቡር የወረዳ አመራሮችና ሰራተኞች በስራ ገበታቸው ተገኝተው ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ለማረጋገጥ እና በስራ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች ካሉም በመወያየት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንደሆነም ነው የተገለፀው።

በዚሁ መሰረት በዛሬው እለት የሱፐርቪዥን ቡድኑ በወረዳ 1፣ ወረዳ 3 እና በወረዳ 9 ድንገተኛ ምልከታ ያደረገ ሲሆን በምልከታው የታዩ ጥንካሬዎችን እንዲሁም የታዩ ውስንነቶችን በተመረከተ ከወረዳ አመራሮች ጋር አጭር ውይይት በማድረግ በቀጣይ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያም የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትምነት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በአጠቃላይ በአስተደደሩ የሚገኙ ተቋማት አመራሮች እና ሰራተኞች ለተገልጋዮች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ቀጣይነት ያለው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ የተገለፀ ሲሆን በሌሎች ወረዳዎችና ሴክተር ተቋማትም መሰል ምልከታዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *