ቢቢሲ የሕዳሴ ግድብን ግዙፍነት እንዴት ገለጸው?

ቢቢሲ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግዙፍነት በገለጸበት ዘገባው፣ “ኢትዮጵያ በአፍሪካ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቧን በያዝነው የፈረንጆቹ መስከረም ወር ታስመርቃለች” ብሏል።

በዓባይ ወንዝ ላይ በ4.6 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ5 ሺህ በላይ ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚያመነጭም ጠቁሟል።

በንፅፅር ሲያስቀምጠውም፣ የግብጹ አስዋን ግድብ እና የአሜሪካው ሁቨር ግድብ ከሚያመነጩት ኃይል ከእጥፍ በላይ የማመንጨት አቅም እንዳለውም ጠቅሷል።

በዘገባው ‘ዊቢዩልድ ግሩፕ’ን ጠቅሶ ስለግድቡ የሚገልፁ የኢንፎግራፊክስ ቁጥራዊ መረጃዎች አስቀምጧል።

5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል እንዲያመነጭ ሆኖ የተገነባ፤ በዓመት 15 ሺህ 700 ጊጋዋት ሰዓት በአማካይ የሚያመነጭ እንዲሁም 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የያዘ መሆኑንም አመላክቷል።

13 ተርባይኖች እንዳሉት፣ ቁመቱ 170 ሜትር፣ ርዝመቱ 1.8 ኪሎ ሜትር እንደሆነ ነው ቢቢሲ በዘገባው የጠቀሰው።

የግድቡን ውኃ የያዘው ንጋት ሐይቅ 246 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው ቢቢሲ በቁጥራዊ መረጃዎቹ ውስጥ አካትቷል።

ኢትዮጵያውን ቦንድ በመግዛት እና በስጦታ መልክ ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማዋጣታቸውን፣ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ 14 ዓመታት መውሰዱን እንዲሁም በየዓመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በግንባታው ላይ መሳተፋቸውንም ቁጥራዊ መረጃው ያሳያል።

ኢትዮጵያ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝ ይጠበቃል።

ግድብ ታዳሽ ኃይልን የሚጠቀም በመሆኑ በዓመት ሁለት ሚሊዮን ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር እንዳይገባ ያደርጋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *