የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ አዲስ ዘመንን አስመልክተው ለሚዲያ አካላት በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ታላቁ ህዳሴ ግድብ ቀደምት አያት አባቶቻችን አባይን የመገደብ ህልም ሲወርድ ሲዋረድ እኛ ጋር ደርሶ እውን ያደረግነው አኩሪ አሻራቸን መሆኑን ገልፀዋል የህዳሴው ግድብ መገባደድ በተለይም በአዲሱ 2018 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓል ጋር ብስራቱ በመያያዙ በአዲስ የመፈጠር ያህል ይቆጠራል ሲሉም ገልጸዋል።
ጠቅላይ አዛዡ አክለውም የታላቁ ህዳሴ ግድብ መላው ኢትዮጵዊያን በአንድ ሃሳብ ፣ በአንድ ዓላማና አመለካከት እንዲሁም በራስ አቅምና በራስ ወጪ ያለ ውጪ ድጋፍ ተገንብቶ ለመጠናቀቅ በመቻሉ ኢትዮጵያውያን የምንጠራበትን አንድነትና ህብረት የበለጠ ያጠናክረዋል ብለው በዚህ አንድነታችንም የውጪ ባዳና የውስጥ ባንዳዎችን አኩይ ሃሳብ ማፍረስ የቻልንበት አኩሪ ገድላችን ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምርቃት ከአዲሱ ዘመን መለወጫ በዓል ጋር በመገናኘቱና የኢትዮጵያ ንጋት ጮራ በልማት ስራዎች እየፈነጠቀበት በሚገኝበት ልዩ ወቅት በመሆኑ ደስታውን እጥፍ እንደሚያደርገው የገለጹት ኮሚሽነሩ በዚህ ታሪክ አሻራ ተሳታፊነት የበቃ ትውልድ አባል ለሆናችሁ መላው ህዝብ በሙሉ አንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ የደስታ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል ።
እኛ የአባይ ልጆች ብቻ ሳንሆን የአባይ ንጉሶች ጭምር ነን ያሉት ኮምሽነር ዓለሙ በህዳሴው ግድብ ያሳየነውን ህብረትና አንድነት በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም አጠናክረን በማስቀጠል ከምንጊዜውም በላይ ልዩ ድባብ የፈጠረውን መጪውን አዲስ አመት ለኢትዮጵያ ብልጽግና ጉዞ አንድ እርካብ መሸጋገሪያ እናድርገው ሲሉም ነው በመልዕክታቸው ያመለከቱት ።


