በዚህም ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሀር ድሬዳዋን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ አስተዳደሩ ስራዎችን በቅንጅት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አመላክተዋል።
አስተዳደሩ ከባለሀብቶች ጋር በጋራ በመሆንም ከተማዋ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋዎች በመጠቀም የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ከንቲባ ከድር የገለፁ ሲሆን በአጠቃላይም ከተማዋን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመጥቀስ ሰፊ ማብራሪያ ሰተዋል።
ድሬ ቀንም ለሊትም እንቅስቃሴ ያለባት ከተማ መሆኗን፣ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በአብሮነት እና በመተሳሰብ እንደሚኖሩባት እንዲሁም የማህበረሰቡ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል የከተማዋን የቱሪዝም ማዕከልነት እንደሚያጠናክረው ከንቲባ ከድር ጠቁመዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ፣ ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ወደ ድሬዳዋ በመምጣት በጋራ አብሮ ለመስራት በማቀዱ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ ድሬዳዋ ያላትን ተፈጥሮአዊ የቱሪዝም ሀብቶች እና ማህበራዊ እሴቶቿን በመጠቀም ለቱሪስት መስህብነት የማዋል ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በከተማዋ የሚመጡ ቱሪስቶችን መያዝ የሚችሉ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንደሚገኙ የተናገሩት ምክትል ከንቲባ ሀርቢ አዳዲስስ ሆቴሎችም በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከአዲስ አበባ ባሻገር በሀገራችን የሚዘጋጁ ትልልቅ ጉባኤዎችን ሌሎች ከተሞች ላይ ለማካሄድ የታቀደ መሆኑን ገልፀው፤ ለዚህም ደግሞ ድሬዳዋ ተመራጭ መሆኗን ተናግረዋል።
ድሬዳዋ በከፍተኛ የልማት ጎዳና ላይ እንደምትገኝ እንዲሁም ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ስራዎችን እየሰራች እንደሆነ ሚኒስትር ድኤታው ጠቅሰው፤ ከተማዋን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እንደ ቱሪዝም ሚኒስትር ስራዎች በጋራ እንደሚሰሩ አመላክተዋል።
ከተማዋን የቱሪዝም ማዕከል የማድረጉ ስራ በዚህ ዓመት እንደሚጀመርና የድሬዳዋን የኮንቬንሽን ማዕከል ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት በርብርብ እንደሚሰራም ሚኒስትር ድኤታው ጨምረው ገልፀዋል።
አስተዳደሩ ከግል አልሚዎች ጋር ተቀናጅቶ እያከናወናቸው የሚገኙ የቱሪዝም ልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ሚኒስትር ድኤታው ያመላከቱ ሲሆን፤ ድሬዳዋን ከኢንደስትሪና ንግድ ማእከልነቷ በተጨማሪ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) የተመራ ልኡካን ቡድን በድሬዳዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል


