የድሬዳዋ ከተማ ዋንጫ/ድሬዳዋ ሲቲ ካፕ የእግር ኳስ ጨዋታ የዕጣ ድልድል ይፋ ሆነ

ለወራት ሲጠበቅ የነበረው “የድሬዳዋ ከተማ ዋንጫ” / “ድሬዳዋ ሲቲ ካፕ” የእግር ኳስ ውድድር የዕጣ ድልድል ዛሬ ከሰዓት በኋላ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ውድድሩም ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

አምስት ክለቦችን የሚያሳትፈው ይህ ውድድር በድሬዳዋ ከተማ ለእግር ኳስ አፍቃሪዎች ደስታን እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

በኢስት ስታር ሆቴል በተካሄደው የዕጣ ድልድል መርሃ ግብር ላይ የውድድሩ አዘጋጆችና አሰልጣኞች እንዲሁም የክለብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ለቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ሳዳት ጀማል የመታሰቢያ የህሊና ጸሎት ተደርጓል።

የድሬዳዋ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስነስርዓት ኃላፊ የሆኑት አቶ ኤርምያስ ሀይሉ ውድድሩ በድሬዳዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው፣ ሁሉም ተሳታፊ ክለቦች ስፖርታዊ ጨዋነትን እንዲያሳዩ አሳስበዋል።

“ይህ ውድድር በድሬዳዋ የእግር ኳስ እድገት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው” ያሉት አቶ ኤርምያስ፣ ለሁሉም ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጎፈሪ ድርጅት የማርኬቲንግና ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሚካኤል ለገሰ በወቅቱ እንዳስታወቁት፣ የውድድሩ አሸናፊ የዋንጫ፣ የወርቅ ሜዳሊያ እና በመቶ ሺህ የሚቆጠር የብር ሽልማት ያገኛል። ሁለተኛ ለወጣው ቡድን የብር ሜዳሊያ የሚበረከት ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ጨዋታ ኮከብ ለሆነ ተጫዋች 15,000 ብር የሽልማት ገንዘብ ተዘጋጅቷል።

በጨዋታው መርሃ ግብር መሰረት ነገ መስከረም 23 በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የመክፈቻ ጨዋታው ይከናወናል።

በወጣው የጨዋታው ዕጣ ድልድል መሰረት

መስከረም 23 (አርብ ):

የመክፈቻ ጨዋታ: ድሬዳዋ ከተማ ከ ጅቡቲ ሪፐብሊካን ጋርድ – ምሽት 11:00

መስከረም 24 (ቅዳሜ)

ድሬ ምርጥ ከ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ – ከቀኑ 10:00

መስከረም 26 (ሰኞ)

ጅቡቲ ቴሌኮም ከድሬዳዋ ከተማ – ቀን 10:00

ጅቡቲ ሪፐብሊካን ጋርድ ከድሬ ምርጥ – ምሽት 12:30

መስከረም 28 (ረቡዕ):

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ ጅቡቲ ቴሌኮም – ቀን 10:00

ድሬዳዋ ከተማ ከ ድሬ ምርጥ (የድሬዳዋ ደርቢ) – ምሽት 12:30

መስከረም 30 (ዓርብ)፡

ጅቡቲ ሪፐብሊካን ጋርድ ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ – ቀን 10:00 ሰዓት

ድሬ ምርጥ ከ ጅቡቲ ቴሌኮም – ምሽት 12:30 ሰዓት

ጥቅምት 2 (የፍጻሜ ቀን):

ጅቡቲ ቴሌኮም ከጅቡቲ ሪፐብሊካን ጋርድ – ቀን 10:00

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ ድሬዳዋ ከተማ – ምሽት 12:30

የውድድሩ ስርዓት በነጥብ ብዙ የሰበሰበው ቡድን አሸናፊ እንደሚሆን በአቶ ኤርምያስ ሀይሉ ተገልጿል።

ይህ የነጥብ ስሌት ውድድሩን ከመጀመሪያው ቀን እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ አስደሳች እና ተንቀሳቃሽ እንደሚያደርገው ይታመናል።

በድሬዳዋ የሚካሄደው ይህ ሲቲ ካፕ፣ የአካባቢውን እግር ኳስ ለማነቃቃት ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ እና በጎረቤት ጅቡቲ ክለቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት እና የስፖርት ትስስር ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

የከተማዋ ነዋሪዎች እና የእግር ኳስ አድናቂዎች ለዚህ ታላቅ የስፖርት ክስተት በጉጉት እየጠበቁ ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *