በድሬዳዋ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ልማታችን እንዲፋጠን ፣ ፍትሀዊነት እንዲሰፍን እና የህዝባችንን መብት ለማስጠበቅ እየሰጡት ካለው የዳኝነት አገልግሎት ባሻገር በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እያደረጉት ያለው የነቃ ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ካሊድ መሐመድ ገለጹ

የድሬዳዋ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፣ የድሬዳዋ ጠበቆች ማህበር ፣ አቃቤያነ ህጎችና ሰራተኞች በራሳቸው ተነሳሽነት ባዋጡት ገንዘብ በወረዳ አራት ዝቅተኛ ደሞዝ ተከፋይ የሆኑ አንዲት ሰራተኛን ቤት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ግንባታ አስጀምረዋል ።

ሁለቱ ፍርድ ቤቶች በ2018ዓ/ም የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በወረዳ 05 እና 08 ካስገነቧቸው ሁለት የአቅመ ደካሞች ቤቶች በተጨማሪ በተቋማቸው ውስጥ ዝቅተኛ ደሞዝ እየተከፈላቸው ከሚሰሩ ሰራተኞች መካከል ከዳኞች፣ አቃቢያነ ህጎችና ሰራተኞች በተሰባሰበ የመዋጮ ገንዘብ የአንድ የፍርድ ቤቱ ሰራተኛ የሆኑ ገለሰብ ቤት ግንባታ ማስጀመራቸውን የገለጹት የድሬዳዋ አሰተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ነጂብ ኢድሪስ ፣ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤታቸውን የገነባንላቸው አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች ከነበረባቸው ችግር ተላቅቀው ስንመለከት የምናገኘው የመንፈስ እርካታ በብዙኃን አነስተኛ አስተዋጾ ለጥቂቶች ግን ሕይወታቸውን ወደ ተሻለ ምእራፍ የሚያሸጋግርና የሚለውጥ ስራ መስራት እንደሚቻል መገንዘባቸው ተነሳሽነቱን እንደፈጠረ ነው የተናገሩት ።

ይህ ወደ ውስጣችን በመመልከት በድሬዳዋ ይግባኝ ሰሚና እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በዝቅተኛ ደሞዝ እያገለገሉ የሚገኙ ሰራተኞቻችንን የመደገፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራችን ወደ ፊት አጠናክረን የምንቀጥልበት ይሆናል ያሉት አቶ ነጂብ ኢድሪስ፣ በዚህ አስደሳች ተግባር ላይ የተሳተፉትን የሁለቱን ፍርድ ቤቶች ዳኞች ፣ አቃቢያነ ህጎች፣ የድሬዳዋ ጠበቆች ማህበር አባላት እና የተቋማቱ ሰራተኞችን አመስግነዋል ።

የድሬዳዋ ጠበቆች ማህበር ምክትል ሰብሳቢ አቶ አማኑኤል ፍሰሐ በበኩላው ማህበራችን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከሚያከናውናቸው ተግባራት ይህ የዛሬው አይነቱ የተለየና ከፍተኛ የመንፈስ እርካታን የሚሰጥ ነው ያሉ ሲሆን ማህበራችን ወደፊትም መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በቤት ግንባታው ማስጀመሪያ ላይ የድሬዳዋ የመጀመረያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ አብዲ፤ ዳኞች ፣ጠበቆች፣ አቃቢያነ ህጎች እና የፍርድ ቤቱ ሰራተኞች እና የወረዳ 04 ስራ አስፈጻሚ አቶ ኡስማኢል አብዱልለጢፍን ጨምሮ የድሬዳዋ ጠበቆች ማህበር አባላት ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *