የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማስገባትና የኢትዮጵያን ስኬት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ እና ተናባቢ ስራ ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ::

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በ2018 የዝግጅት ምዕራፍ የስትሪሚንግና ክላስተር ኮሚቴ ውይይት መድረክ በትላንትናው እለት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በ2018 የዝግጅት ምዕራፍ የስትሪሚንግና ክላስተር ኮሚቴ ውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፥የንግድ፣ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሐርቢ ቡህ እንደተናገሩት አስተዳደሩን የንግድና ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የአምራች ዘርፉን በጋራ መደገፍ የግድ እንደሆነ አሳስበዋል።

አቶ ሐርቢ አክለውም የአምራች ኢንዱስትሪው ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር እስከ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ገልፀው ይህንን አቅም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም በፋይናንስ በመሰረተ ልማት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን በጋራ በመስራት መፍታት ይገባል ብለዋል።

የንግድ፣ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንትፐቢሮ ምክትል እና የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታርም በበኩላቸው በ2018 በጀት ዓመት የኢንዱስትሪውን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአንድ አቅጣጫ በመንቀሳቀስ ለተሻለ ውጤት እንዲሰሩ የሚያስችሉ እቅዶች መያዛቸውን አብራርተዋል።

የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማፋጠን የፈጠራ ስራዎችን ማበረታታት የሰው ኃይል ክህሎትን ማሳደግ እና የፋይናንስና የመሰረተ ልማት አቅርቦት ማሻሻል በዚሁ የተቀናጀ እቅድ ውስጥ የተካተቱ ናቸው።

በአጠቃላይ የድሬዳዋ አስተዳደር በ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ማዕቀፍ ውስጥ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለመደገፍ እና አስተዳደሩን ወደፊት ለማስኬድ የጋራ እና የተቀናጀ ስራ የመፍትሄው ቁልፍ መሆኑን በመድረኩ አፅንዖት ተሰጥቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *