“ዲጂታላይዜሽንና ፈጠራ ለጠንካራ የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል 13ኛው የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ ዓመታዊ ጉባኤ በድሬዳዋ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።
በዚህም በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር
ጉባኤው በድሬዳዋ በመካሄዱ የተሰማቸውን ደስታ በመግለፅ፤ ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ለአስተዳደሩ ብሎም እንደ ሀገር የተጣለበትን የማህበረሰብ ጤና የማስጠበቅና የዜጎች ህክምና የማግኘት መብት እንዲከበር የማድረግ ስራ በሰፊው እየሰራ እንደሚገኝም ክቡር ከንቲባ ከድር አብራርተዋል።
ከንቲባ ከድር አያይዘውም የደምና ሕብረህዋስ ባንክ አገልግሎቱን ከማሻሻልና ከማሳደግ በተጨማሪም በድጂታላይዜሺን እና ፈጠራ ላይ የተመስረተ የአሰራር ስርአትን ዘርግቶ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው ይህም የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ በበኩላቸው የደምና ሕብረህዋስ ስራዎች ከሰዎች ህይዎትና ብርሃን ጋር የተሰናሰሉ በመሆናቸው ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረው፤ እነዚህ ስራዎች ከእጅ ንክኪ ነፃና ዲጂታላይዝ የማድረጉ ስራ ተጠናአክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
የጤና ሚኒስቴር ለዲጂታላይዜሺን እና ለፈጠራ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ በመሆኑ የአገልግሎት ዘርፉን ለማዘመን እና ለማጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ሚኒስትር ድኤታዋ አመላክተዋል።
ሀገር አቀፍ ዲጂታል የጤና ፖሊሲን ከመተግበር አንፃር የኢትዮጵያ ደምና ሕብረህዋስ ባንክ አገልግሎት እንደ ተቋም ከደም አሰባሰብ እስከ ስርጭት በዘርፉ ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ዲጂታል አሰራሮችን በስፋት ስራ ላይ አውሎ እየሰራ መገኘቱንም ሚኒስትር ድኤታዋ ጠቅሰው ይህም በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
“ድጅታላይዜሽን እና ፈጠራ ለጠንካራ የደምና ሕብረህዋስ ባንክ አገልግሎት ” እውን ለማድረግ የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ደም እና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው ናቸው።
የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ ድሬዳዋ የንግድ፣ የኢንደስትሪና የኢንቨስትመንት ማዕከል በመሆኗ የሰዎች እንቅስቃሴ የሚበዛ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም ለማህበረሰቡ ጤና ከፍተኛ ትኩረት ተሰቶ ስራዎች በሰለጠኑና ብቃት ባላቸው የሰው ሀይል እንዲሁም በዘመናዊ አሰራሮች ታግዘው እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ጉባኤው ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ይሆናል።


