ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ከኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ ጋር በጋራ በመሆን በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ የዘመናዊ የደም ተላላፊ በሽታዎች መመርመሪያ ማሽንን በዛሬው ዕለት መርቀዋል።
ከዚህ ቀደም ማሽኑ በአስተዳደሩ ባለሞኖሩ ናሙናዎች ወደ ሌሎች ከተሞች እየተላኩ ምርመራ የሚደረግ ሲሆን ይህም ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ከንቲባ ከድር የተናገሩ ሲሆን፤ አሁን ማሽኑ በድሬዳዋ አስተዳደር መኖሩ ብዙ ናሙናዎችን በሰዓታት ውስጥ መመርመር እንደሚያስችል በተጨማሪም ለተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
ለማሽኑ የሚያስፈልጉ ግብአቶች ከግል ተቋማት ጋር በመቀናጀት የተሸፈነ መሆኑን ክቡር ከንቲባ ከድር ያመላከቱ ሲሆን በዚህም ተሳትፎ ላደረጉ ተቋማት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ በበኩላቸው ማሽኑ ተላላፊ በሽታዎችን ከእጅ ንክኪ ነፃ በሆነ መንገድ በፍጥነት እንደሚመረምር ገልፀው ይህም ለተገልጋይም አስተማማኝ ህክምና ለመስጠት እንደሚያስችል አመላክተዋል።
ማሽኑ በድሬዳዋ መኖሩ ከድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች በተጨማሪ ለአጎራባች ክልሎችም ከፍተኛ አገልግሎት እንደሚሰጥ ሚኒስትር ድኤታዋ ተናግረዋል።
በተያያዘም ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሀር ከኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ደም እና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው እና ከድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ ጋር በጋራ በመሆን የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ የተቀናጀ ህንፃ ግንባታን ለማከናወን የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።


