የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ህብረተሰቡ ህጻናት ልጆችን የፖሊዮ ክትባቱን እንዲወስዱ በማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪውን አቅርቧል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ከሁለም ቀበሌዎች ለተወጣጡ ባለድርሻ አካላት በፖሊዮ ክትባት አስፈላጊነትና በቅንጅታዊ አሰራር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል ።
እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ከ97 ሺህ በላይ ህፃናትን በዘንድሮ ሶስተኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በአስተዳደሩ በሁሉም ወረዳዎች እና የገጠር ቀበሌዎች ለመከተብ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዩሱፍ ሰኢድ በስልጠናው መድረክ መክፈቻ ላይ ተናግረዋል።
“ክትባት ለጤናማ ማህበረሰብ” በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 30 ፥ 2018 ዓ.ም ጀምሮ ቤት ለቤት ለሚሰጠው የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ህብረተሰቡ ለጤና ባለሞያዎች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ጤናማ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን ትብብር በማድረግ ሀገራዊ የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ዩሱፍ ገልጸዋል።
ቤት ለቤት ከሚደረገው የክትባት ዘመቻ በተጨማሪ በአስተዳደደሩ በ3 የመንግስት ሆስፒታሎች ፣ በ16 ጤና ጣቢያዎች እና በ37 ጤና ኬላዎች የፖሊዮ ክትባቱ አንደሚሰጥ አውቆ ህብረተሰቡ እድሜያቸው ለክትባት የደረሱ ህጻናት ልጆቹን እንዲያስከትብ በመድረኩ ጥሪ ተላልፏል ።


