በአይነቱ ለየት ያለዉና በድሬዳዋ እግር ኳስ ታሪክ ዉስጥ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የድሬ ካፕ የድሬደዋ ከተማ ዋንጫ በመጨረሻም በድሬ ከነማ ቡድን አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
በ5 ክለቦች መካከል ፥ ከሀገር ዉጭ ፣የጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ክለቦች የሆኑትን ጅቡቲ ቴሌኮምንና ጅቡቲ ሪፐብሊካንን፣ከሀገር ዉስጥ የፕሪሚየር ሊግ ተወካይ የሆኑትን ወልዋሎ አድግራት ዩንቨርስቲን እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማን እና ከነዚህ በተጨማሪ ለውድድሩ የተዋቀረውን የድሬ ምርጥ ቡድንን ለሳምንታት ሲያፋጥጥ የቆየው የድሬ ካፕ የድሬደዋ ከተማ ዋንጫ በመጨረሻም ድሬደዋ ከተማን አንግሶ መቋጫዉን አግኝቷል።
በዉድድሩ ብዙ ነጥብ የሰበሰበ ቡድን ሻምፒዮና የሆነ ሲሆን በዚህም መሰረት ድሬዳዋ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ጫወታ ብቻ አቻ ተለያይቶ ቀሪዎቹን ሶስት ጫወታዎች አሸንፎ በ10 ነጥብ ሻምፕዮን ለመሆን በቅቷል።
ድሬደዋ ከተማ በመጨረሻዉ ጫወታው ዛሬ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲን ክለብን በጠባብ ዉጤት አሸንፎ ነዉ ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠዉ። በዉድድሩ ጅቡቲ ቴሌኮም በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ በ8 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ በ7 ነጥብ ሶስተኛ ፣ጂቡቲ ሪፐብሊካን በ3 ነጥብ አራተኛ እንዲሁም በዉድድሩ ምንም ነጥብ መሰብሰብ ያልቻለዉ ድሬ ምርጥ ቡድን መጨረሻ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
በዉድድሩ ተሳታፊ የነበረዉ ድሬ ምርጥ ቡድን ምንም እንኳን አንድም ጨዋታ ማሸነፍ ባይችልም ነገር ግን ልምድ ይወስድበታል ተብሎ ይጠበቃል ፤ ከዚህም ባሻገር ውድድሩ በድሬዳዋ እግር ኳስ እድገት ዉስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረዉም ይጠበቃል። እንዲሁም ለተተኪ ታዳጊዎች እድልን መፍጠር እንደሚችልም ይታመናል።
ድሬዳዋ ከተማና ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ክለቦች ከዚህ ዉድድር በእጀጉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይታመናል፤ ምክንያቱም የኢትዩጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከመጀመሩ አስቀድሞ ዉድድሩን ማድረጋጀዉ እንደ ጥሩ ዝግጅት ይጠቅማቸዋልና፤ የጂቡቲ ክለቦችም በዚሁ ልክ ተጠቃሚ ናቸዉ።
ከእግር ኳስ በዘለለ ዉድድሩ ሀገራዊ አንድነትና ወንድማማችነትን እንደሚያመጣም ከፍተኛ የሆነ ተስፋ ተጥሎበታል ። ድሬዳዋ የእግር ኳስ መናገሻ መሆኗንም ከማስተዋወቅ አንፃር ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
የድሬዳዋ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ ይህ ዉድድር መደረጉ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት በመግለፅ አይኖች ሁሉ ድሬደዋን እንዲመለከቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለዉ ብለዋል በቀጣይም ከዚህ በበለጠ መልኩ በተለይ ዳስፖራዉን ተሳታፊ ያደረገ ዉድድር እንደሚከናወን ጠቁመዋል።


