ድሬዳዋ እና የፈረንሳይ ሌጉ ከተማ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር በማጠናከር በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ

የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ በፈረንሳይ ሌጉ ከተማ ከንቲባ ሊዮኒዳስ ሰርጅ ከተመራ ልኡካን ቡድን ጋር የሁለቱን ከተሞች እህትማማችነት ለማጠናከር እና በቀጣይ በጋራ አብሮ ለመስራት በሚቻልባቸው ነጥቦች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱም ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ለእንግዶች የእንኳን ደና መጣችሁ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ በኢትዮጲያ እና በፈረንሳይ መካከል ጠንካራ ወዳጅነት እና ትብብር መኖሩን ገልፀዋል።

ምክትል ከንቲባ ሀርቢ አያይዘውም በድሬዳዋ በ1908 ዓ.ም ስለተገነባው እና በርካታ ተማሪዎችን ስላፈራው አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ትምህርት ቤት እንዲሁም ስለ ምድር ባቡር ድርጅት ማብራሪያ በመስጠት በአጠቃላይም ስለድሬዳዋ አስተዳደር ገለፃ አርገዋል።

ድሬዳዋ እና የፈረንሳይዋ ሌጉ ከተማ አጋርነት የባህል ልውውጥን ከመፍጠር በተጨማሪም በትምህርት እና በኢኮኖሚው ዘርፍ በጋራ ለመስራት ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ተናግረው፤ የከተሞቹ እህትማማችነት መጠናከር ለዘላቂ ልማት፣ ፈጠራን ለማሳደግ እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማፋጠን እንደሚያስችል አብራርተዋል።

የዛሬው መድረክም ከተሞቹ እርስ በርስ እንዲማማሩ፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን እንዲለዋወጡና አዳዲስ እድሎችን ለመፍጠር ጉልህ ሚና እንዳለው ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ተናግረዋል።

የፈረንሳይዋ ሌጉ ከተማ ከንቲባ ሊዮኒዳስ ሰርጅ በበኩላቸው በድሬዳዋ አስተዳደር ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን በማቅረብ፤ የድሬዳዋን እና የፈረንሳይን የእርስ በእርስ ትስስር የማሳደግ እና የማጠናከር ስራዎች እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

ከንቲባው አያይዘውም በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ድሬዳዋን ሊያስተዋውቁ የሚችሉ ስራዎች በስፋትና በቅንጅት እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

በመጨረሻም ከንቲባው ድሬዳዋ እና ሌጉ ከተማ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር በማጠናከር በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *