“ከአደጋ ይልቅ ለአደጋ ስጋት አይበገሬነት ግንባታ ትኩረት እንስጥ” በሚል መሪ ቃል የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀን አከባበርን አስመልክቶ የተዘጋጀ መድረክ በድሬዳዋ ተካሂዷል።
የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ48ኛ ጊዜ፥በሀገራችን ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ እንዲሁም በአስተዳደሩ ለ11ኛ ጊዜ ዘንድሮ እንደሚከበር ተገልጿል።
በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ እና በከንቲባ ጽ/ቤት የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ዶ/ር ሰይፉ ታደሰ እንደ አጠቃላይ ሀገራችን ካላት መልክዓ ምድር አቀማመጥ እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ጋር ተያይዞ ለአደጋ ተጋላጭ መሆኗን ጠቅሰው አስተዳደሩ ይህን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ የቅድመ መከላከል ስራ በመስራት የሚታይ ውጤት አስገኝቷል ብለዋል።
ለዚህ ማሳያ እንዲሆን በ1998 ዓ.ም በድሬዳዋ ተከስቶ የነበረውን ጎርፍና ያስከተለውን መጠነ ሰፊ ጉዳት ዶ/ር ሰይፉ አስታውሰው ሆኖም ግን ከዚያ በኋላ በአስዳደሩ አመራር አስተባባሪነትና በአርሶአደሩ ጉልበት የተሰሩ የተፋሰስ ስራዎች ዳግም መሰል አደጋ እንዳይከሰት ከተሰሩ ስራዎች እጅግ ውጤታማዎቹ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ዶ/ር ሰይፉ አክለውም ለአደጋ ስጋት ቅነሳ የሚደረግ ቅድመ ድጋፍና መጠባበቂያ ሀብት በአደጋ ወቅት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ እንዳይከሰት በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለው ለዚህም ለአደጋ አይበገሬ ማህበረሰብ ግንባታ ላይ ብሎም የሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ንቅናቄ ላይ በቀጣይ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ዘሪሁን ዘውዴ በበኩላቸው ለበርካታ ዓመታት በአደጋና ስጋት መከላከል በኩል ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ምላሽ ላይ የመረባረብ የስራ አካሄድ ዋጋ ከማስከፈል በላይ ተረጂነትና ልመና ላይ ተገን አድርገን ለውጥ እንዳናመጣ መሰናክል ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።
ቅድመ ሀብትና ፈንድ በማሰባሰብ በውስጥ ድጋፍ አደጋና ስጋት ቅነሳ ስራን የመከወን አቅም መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ሀላፊው የዘንድሮው የአደጋ ስጋት ቅነሳ በአይበገሬነት መርህ ላይ ማተኮሩ ለሶስተኛ ትውልድ አብዮተኛ ለመሆን ለሚደረገው ቀጣይ ስራ ስንቅ የሚሆን መሆኑን አመላክተዋል።
አቶ ዘሪሁን በኢትዮጵያ 40 ሚሊየን ዜጎችን ከተረጂነት ለማላቀቅ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በእስካሁኑ ሂደት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውን ጠቅሰው በተለይ በድሬዳዋ በአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀድሞ መከላከል በኩል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በተሞክሮነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነርን በመወከል በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዱሰላም ዩሱፍ ለአደጋ ስጋት ቅነሳ የሚደረግ ኢንቨስትመንትን በማጎልበት ለአይበገሬነት ማህበረሰብ ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለው ይህም ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ዕውን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
በመድረኩ ከተለያዩ ሴክተር ተቋማት ተጠሪ የሆኑ አካላትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ዓለም ዓቀፍ የአደጋ ስጋት ቀን የተመለከተ ሰነድ በዶ/ር ዮናስ ታደሰ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።


