በባለፉት ሶስት ወራት ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን አስታውቋል።
የትምህርትና ስልጠና ደንበኞች አገልግሎት ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አክሊለ ታጠቅ በዛሬው እለት ለሚዲያ አካላት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ባለስልጣን መስሪያቤቱ በባለፉት ሶስት ወራት 2.5 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 1.7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብን እና በዚህም የእቅድን 85 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።
አስተዳደሩ የግብር አሰባሰብ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ በማዘመን የገቢ አሰባሰብ ችግሮች በየደረጃው እየተቀረፉ መምጣታቸውንም ገልጸዋል።
ግብርን በወቅቱ መክፈል የዜግነት ግዴታ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አክሊለ ግብር ከፋዮች ወደ ተዘጋጀላቸው ማዕከላት በመቅረብ ግብርን በወቅቱ መክፈል እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
በተሻሻለው የግብር አዋጅ 1395/2017 ማሻሻያ በተደረገባቸው የግብር አከፋፈል አፈጻጸም ላይም በአማራጭ አነስተኛ ግብር አከፋፈል ስርዓት 2.5 % አነስተኛ ግብር አከፋፈል ስርዓት መወሰኑ፣ግዢን በሚመለከት የጥሬ ገንዘብ ግብይት ከ50 ሺ ብር በላይ ግዢ መፈጸም እንደማይቻል በአዋጁ መደንገጉን እና ህብረተሰቡ ይህን ተገንዝቦ መተግበር እንደሚገባ አቶ አክሊለ አስረድተዋል።
በተጨማሪም የግብር ከፋዮች ደረጃም ቀደም ሲል የደረጃ ሀ፣ለ እና ሐ ግብር ከፋዮች በተሻሻለው የግብር አዋጅ ቁጥር 1395/2017 መሰረት በደረጃ ሀ እና ለ ብቻ መወሰኑንም ሀላፊው ጨምረው ገልጸዋል።


