ለብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና የፓርቲው ፕሬዚዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት የሥራ መመሪያ በስኬት ፍፃሜውን ማግኘቱን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፓርቲው ዋናው ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ አስታወቁ።
“በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሐሳብ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ከጥቅምት 19 እስከ 30 በአዳማ እና በአዲስ አበባ ከተሞች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ሲሰጥ ቆይቷል።
በሥልጠናው ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ የፓርቲው አመራሮች እንደተሳተፉበት አቶ አደም በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አመላክተዋል።
ሥልጠናው የአስተሳሰብ አንድነት ከመፍጠር እና የተግባር አፈፃፀምን ከማላቅ አኳያ እጅግ ከፍተኛ ፋይዳ የተገኘበት እና ፓርቲው እውነተኛ የኅብረ ብሔራዊነት ተምሳሌት መሆኑም በተጨባጭ የተንፀባረቀበት ነበር ሲሉም ገልጸዋል።
የሥልጠና መርሀ ግብሩ ከዝግጅት እስከ ገለጻ፣ የቡድን ውይይት፣ ተሞክሮ ልውውጥ፣ የልማት ሥራዎች የመስክ ጉብኝት እና ማጠቃለያ ድረስ ዓላማውን በሚገባ አሳክቶ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታውን ለተወጡ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በዚህም አስተባባሪዎችን፣ አሰልጣኞችን፣ አወያዮችን፣ የፀጥታ ተቋማትን፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና ልዩ ልዩ ተቋማቱን አመስግነዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የሥልጠናው ተሳታፊ አመራሮችም ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስገና ያገኙ ናቸው።


