አንጋፋውን የኮኔል አካባቢ ታሪኩን በጠበቀ መልኩ በኮሪደር ልማት መልሶ በማልማት ምቹ እና ሳቢ የማድረግ ስራ በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚጀመር ተገለፀ።

የኮኔል የኮሪደር ልማት ኮሚቴ በተዘጋጀው የአካባቢው ዲዛይን ዙሪያ ከነዋሪው ጋር ውይይት አካሄደ።

የድሬዳዋ እምብርት እና የከተማዋ የዘመናዊነት መገለጫ የሆነው የኮኔል አካባቢ እድሜ ጠግብ እና በርካታ የንግድ ቤቶች ያሉበት በመሆን ይታወቃል ።

በከተማው እየተተገበረ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ኮኔልን ታሪካዊነቱን በጠበቀ መልኩ ለማልማት የሚያስችል ውይይት ከነዋሪው ጋር ተደርጓል።

የቀበሌ 06 ሰፈር የኮሪደር ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የወጣቶች እና ስፓርት ኮሚሸን ኮሚሽነር አቶ ካሊድ መሀመድ የከተማዋ የዘመናዊነት መገለጫ የሆነውን ይህን አካባቢ ጌዜውን የዋጀ ምቹ እና ለንግድ የተመቸ ለማድረግ የሚያስችል ዲዛይን መዘጋጀቱን አስታውቀው የኮሪደር ልማቱ የሰፈሩን ገፅታ ጥንታዊ ታሪኩን ሳይለቅ ከማዘመን ባለፈ በሰፈሩ የሚታየውን የጎዳና ተዳዳሪነት እና ስራ አጥነትን የሚቀርፉ ስራዎች ይከናወኑበታል ብለዋል።

አቶ ካሊድ አክለውም በውይይቱ ነዋሪዎቹ ለአካባቢው መልማት ያላቸውን ተባባሪነት አመስገነው ስራውን በተቀመጠው 20 ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ እና የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ከንፍ ፅ/ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ሁኩሚያ መሀመድ በበኩላቸው በውበቷ የምትታወቀው ከተማችን መገለጫ የሆነው የኮኔል ሰፈርን የበለጠ ሳቢ እና ዘመናዊ የማድረጉ ስራ መንግስት እና ህብረተሰብ በመተባበር የሚሰሩት እንደመሆኑ መጠን ውይይቱ በኩነቱ ላይ የነበሩ ብዥታዎችን በመቀረፍ ስራው በተያዘለት ግዜ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጋል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የኑሯቸው መሰረት የሆነው ሰፈሩ በኮሪደር ልማቱ መካተቱ የበለጠ ተመራጭ እና የንግድ ማዕክልነቱን እንደሚያጠናከረው ገልፀው ስራው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሀላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *