የዘንድሮው የአለም የፀረ ሙስና ቀን “ትውልድን በስነ ምግባር ፤ ተቋምን በአሰራር! ” በሚል መሪ ቃል ለ22ተኛ ጊዜ እየተከበረ ሲሆን የአለም የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን ደግሞ ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽን ዘላቂነት ማረጋገጥ በሚል መሪ ቃል በአለም አቀፍ ደረጃ ለ38 ኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ37 ኛ ጊዜ በአስተዳደራችን ድሬዳዋ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ መሆኑ ይታወቃል።
በድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በተዘጋጀው የመማማሪያ መድረክ ላይ የኤች አይ ቪ ተጋላጭነትን መቀነስና የተቋማት አገልግሎት አሠጣጥና የሙስና ተጋላጭነትን መከላከል በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በውይይት መድረኩ የተገኙት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀ እንዳሉት በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድን በመፍጠር ሙስናን ለሚፀየፍ ከዚሁ ጐን ለጐን ደግሞ ጤናውን በመጠበቅ ለነገ የሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ የበኩሉን ድርሻ የሚወጣ ጤናማ ዜጋ መፍጠር ያስፈልጋል።
አቶ ብሩክ አያይዘውም ይህንን ተግባር መሸከም የሚችል የተግባቦት ሠው መሆን እንደሚገባና በሙስናም ሆነ በኤች አይ ቪ ኤድስ ዙሪያ የማህበረሰቡን እሳቤ ከመለወጥ አንስቶ እስከ መልካም ምግባር መትከል ድረስ ሰፊ ስራዎች ይጠብቁናል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ በሁለቱም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ አስተያየት በቢሮው ሠራተኞች የተሠጡ ሲሆን ከመድረኩም ምላሽ ተሠጥቶባቸዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መዋቅራዊ ባለሞያ አቶ ዮናስ ሰለሞን ከቤቱ ለተነሡት ጥያቄዎች ምላሽ በሠጡበት ወቅት በተለይም ከኮንዶም ስርጭት ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር እጥረት መኖሩን በመጠቆም ይህም የተፈጠረው ከጥራት ጋር የተወስነ ችግር ተፈጥሮ ስለነበር መሆኑን ግልፅ በማድረግ በቀጣይ ይሄንን ስርጭት ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡


