”በመደመር መንግስት ዕይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ ሲሰጥ በነበረው የስልጠና ማጠቃለያ ላይ ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሠጡ የስራ አቅጣጫዎች መሠረት በተመረጡ ዘርፎች ተግባራዊ ለማድረግ የተዘጋጀ የ100 ቀን እቅድ አተገባበር ተገምግሟል።
በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በአስተዳደሩ ተጨባጭ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ገምጋሚ ቡድን በድሬዳዋ አስተዳደር የተከናወኑ የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎችን በዛሬው ዕለት ገምግሟል።
በዚህም በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ከታህሳስ 1/2018 ዓ.ም እስከ መጋቢት 10/2018 ዓ.ም የሚተገበር ዕቅድ መሆኑን ገልፀው፤
አስከ አሁን በተሰሩ ስራዎች የታዩ ጠንካራ ጎኖችን ማጎልበት እና ክፍተቶችን ለማረም መረባረብ እንደሚገባ አመላክተው እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት በተለይም ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ይሱፍ በበኩላቸው የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን በጥራት እና በፍጥነት ማከናወን እንደሚገባ፣ የኮሪደር ልማቱን በሚመጥን መልኩ በግሉ ሴክተር ሆቴሎችን ለመገንባት ፈቃድ ተሰቷቸው እስካሁን ወደ ስራ ያልገቡ ወደ ስራ እንዲገቡ፣ አገልግሎት አሰጣጥን ከማቀላጠፍ አንፃር የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ስራዎችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ቅንጅታዊ አሰራርን በማሳደግ ኮትሮባንድን መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የአስተዳዳሩን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የተዘጋጀውን የትግበራ እቅድ የሱፐርቪዥን ቡድን አባላቱ በዝርዝር የተመለከቱ ሲሆን በጥንካሬና በውስንነት የታዩ ነጥቦችን እንዲሁም በእቅዱ ሊካተቱ የሚገባቸውን ተጨማሪ ነጥቦችንም ጠቁመዋል።


