በድሬዳዋ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ የከተማዋን አዲስ ገጽታ በመቀየር ለነዎሪዎቿ ምቹ እንድትሆን ማስቻሉን ያየንበት እና የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራን በማስፋፋት እና በማሳመር ድጋፍ እያደረግን ነው ሲሉ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
እየተሰሩ ያሉት የኮሪደር ልማት ስራዎች የከተማዋ ዳግም ውልደት የፈጠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት ነዋሪዎችን ተጠቃሚ በማድረጉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
የድሬዳዋ የወጣቶች እና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ካሊድ መሀመድ አስተዳደሩ የኮሪደር ልማት ስራ በጥራት እና በፍጥነት የእግረኛ መንገዶችን ፣የማስዋብና የማስጌጥ እንዲሁም የህጻናት መዝናኛዎች እንዲገነቡ በማስቻሉ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።
የድሬዳዋ ኮኔል መንገድ፣ ቀፊራ ኪነ ህንጻዎች ታሪካዊ ስፍራዎች እንደመሆናቸው ታሪካዊ ቅርሳቸውን ሳይቀይሩ የማስዋብ እና የማስጌጥ ስራዎች ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በከተማዋ የሚገኙ ቅርሶችን እና ጥንታዊ ሕንፃዎችን በማስዋብ እና በማልማት የከተማዋን የቱሪስት መስህብነት የበለጠ በሚያሳድግ መልኩ እንደሚካሄድም ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት ስራዎች በተጀመረባቸው ቦታዎች በቅድሚያ የአካባቢውን ነዋሪ ህብረተሰቡ ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ የተጀመረ መሆኑን እና ልማቱን በመደገፍ ቁርጠኝነታቸውን ያሳዩበት መሆኑን ደግሞ የወረዳ 6 አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ቢፍቱ መሀመድ ገልጸዋል።


