የድሬዳዋ አስተዳደር ሰላምን በላቀ ጀግንነትና የአመራር ጥበብ በማስጠበቅ ብሎም ግዳጆችና ተልዕኮችን በብቃት ለመሩና ለፈፀሙ ጀግኖች፣ ተቋማትና ደጋፊ አካላት የዕውቅናና የምስጋና መርሃ-ግብር ማምሻውን አካሂዷል።
በቅርቡ የኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን ድሬዳዋን ጨምሮ በምስራቅ አጎራባች ክልሎች የሽብር ስራዎችን በመስራት ሰላምና ፀጥታን ለማደፍረስ ሲንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን፤
ድሬዳዋን ጨምሮ የምስራቅ ኢትዮጵያ ጥምር የጸጥታ ኃይል በጀግንነት በሽብር ቡድኑ ላይ በወሰደው ጠንካራ እርምጃ የሽብር ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ በመደምሰስ ሲንቀሳቀስበት የነበረውን አካባቢ ወደ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ መመለስ ተችሏል።
በዚህም በእውቅናና በምስጋና መርሃ-ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የድሬዳዋ አስተዳደርን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ በግዳጅ ላይ የላቀ ጀግንነት ላበረከቱ የጸጥታ ኃይሎች፣ በየደረጃ ለሚገኙ የፖሊስና የሚሊሻ አመራርና አባላት እንዲሁም በአጠቃላይ ተሳትፎ ላደረጉ አካላት እውቅና በመስጠት አስፈላጊ መሆን ገልፀዋል።
በዘመቻው ላይ እስከ ህይወት መስዋትነት ለከፈሉ የጸጥታ አባላት ቤተሰቦች አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እና እገዛ ማድረጉን ክቡር ከንቲባ ከድር ተናግረው ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
በከፍተኛ ርብርብ የጠላት ፍላጎት ከንቱ በማድረግ የአስተዳደሩን ሰላም ያስጠበቁ ጀግኖችን ማመስገን ይገባል በማለት ክቡር ከንቲባው ተናግረዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ፣ ፀጥታ እና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱሰላም አህመድ በበኩላቸው አስተዳደሩ ባለፉት የለዉጥ ዓመታት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሲሰራ የቆየ መሆኑን ገልፀው በዚህም ዛሬ ላይ ለሌሎች አካባቢዎች ምሳሌ ጭምር መሆን ያስቻለ ሰላም ብሎም የህዝቦች አብሮነትና ወንድማማችነትን ይበልጥ መገንባትና ማስቀጠል መቻሉን ገልፀዋል።
በመጨረሻም ኃላፊው የዛሬዉ መርሃ-ግብር ግዳጆችና ተልእኮዎችን በላቀ ብቃት የተወጡ ጀግኖችን ከማመስገን በተጨማሪ ገጥመው ከነበሩ ችግሮች በመማር ይበልጥ በፅናት መቆማችንን የምናውጅበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በመርሃ-ግብሩ በጀግንነት ሰላም ላስጠበቁ አካላት በሙሉ የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል።


