በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሀገሪቱ የኃይል ትሥሥር መቶ በመቶ እንዲረጋገጥ ይሰራል፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በመላው ኢትዮጵያ ያለው የኃይል ትሥሥር መቶ በመቶ እንዲረጋገጥ ይሰራል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትልም እውን እንዲሆን እና ዕድገት እንዲረጋገጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ማዳረስ ወሳኝ ነው፡፡

የዲጂታል 2030 መጀመር ይፋ በሆነበት መድረክ ላይ በተካሄደው ውይይት፤ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ሳይሟላ የሚረጋገጥ እድገት እንደማይኖር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በአንድም በሌላም አማራጭ ተደራሽ የሚሆነው የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲዳረስ በመላው ሀገሪቱ የኃይል ትሥሥር መፍጠር ወሳኝ ስለመሆኑም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

ይህም ፍሬያማ እንዲሆን የኃይል ትስስር የሚፈጠርባቸው የሚኒ ግሪድ (አነስተኛ የኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ)፣ ኦፍ ግሪድ (ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ጋር ያልተገናኘ፣ ሙሉ በሙሉ በራሱ ኃይል የሚሰራ) እንዲሁም በፀሐይ ኃይል የሚሰራ አማራጭ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው የተናገሩት፡፡

የኤሌክትሪክ ተደራሽነት የሚረጋገጥበት ትስስር ዜጎች እንደ ዜጋ ማግኘት ላለባቸው ተጠቃሚነት እና ዕድል ምሰሶ ሲሆን ሁሉም ዜጋ በእኩል የመማር፣ የሥራ ዕድል የማግኘት፣ የመታከም እና መሰል ተጠቃሚነቶች አካል የመሆን መብት የሚያረጋግጥበት ነው፡፡

በተለይም የኤሌክትሪክ አገልግሎት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ምግብ በመሆኑ፣ ያለኃይል ትሥሥር እውን የሚሆን የዲጂታል ንቅናቄ እንደማይኖር እሙን ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *